በጋምቤላ ከተማ ባለፈው ካለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ የተከሰቱ የጸጥታ መደፍረሶችን “በማስተባበር” እና “በመሳተፍ” የተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ አራቱ የፖሊስ አባላት መሆናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ ከዋሉት ግለሰቦች አምስቱ፤ መስከረም 23፤ 2019 በጋምቤላ ከተማ ጥቃት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል። ከሁለት ሳምንት በፊት በከተማይቱ በተለምዶ 8100 ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት፤ በአራት “ንጹሃን ዜጎች” ላይ ጉዳት ደርሷል።
በጥቃቱ ከተሳተፉት መካከል ግለሰቦች መካከል አንደኛው በክልሉ ፖሊስ ስር ያለው የአድማ ብተና ኃይል አባል እንደሆነ ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው ይፋ አድርጓል። ይህንን የፖሊስ አባል ጨምሮ ጥቃት ፈጻሚዎችን “በማጓጓዝ እና በማገዝ ተባብረዋል የተባሉ” አራት የባጃጅ አሽከርካሪዎች እና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለጸው ሌሎች ዘጠኝ ግለሰቦች፤ የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ጥቅምት 4፤ 2019 በጋምቤላ ከተማ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ መሆናቸውንም ኮሚሽኑ ጠቁሟል። በዚሁ ዕለት በከተማይቱ ግጭት የተቀሰቀሰው፤ ማክሰኞ ጥቅምት 3፤ 2019 ምሽት በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው እስካሁንም በይፋ ያልተገለጸ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
ጥቃቱ የተፈጸመው “ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት” መሆኑን በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ የነበረው የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፤ ከጥቅምት 4 ጀምሮ “ላልተወሰነ ጊዜ” ተግባራዊ የሚደረግ የሰዓት እላፊ ጥሏል። ከምሽት 12 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት በሚቆየው በዚሁ የሰዓት ገደብ ውስጥ፤ የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ “በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን” ኮሚሽኑ በወቅቱ ገልጿል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በዚሁ መግለጫው፤ በከተማይቱ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙት አካላት “በማጣራት ለህግ ለማቅረብ” ከፌዴራል እና ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በተጠናከረ ሁኔታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጾ ነበር። ኮሚሽኑ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 11፤ 2019 ባወጣው መግለጫ፤ ከክልሉ የጸጥታ ግብረ ኃይል ጋር በመቀናጀት ባካሄደው “የህግ ማስከበር ዘመቻ” “በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን” አመልክቷል።
በዚህ ዘመቻ ከጥቃት ፈጻሚዎቹ ጋር “በተለያዩ መንገዶች ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ” ሶስት መደበኛ የፖሊስ አባላት በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። በጋምቤላ ከተማ “ጥቃቶች እንዲፈጸሙ እና ሰላም እንዳይሰፍን ሲያስተባብር ነበር የተባለ” አንድ ግለሰብም እንደዚሁ መያዙን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን “ግጭት ለማባባስ እና የጦር መሣሪያዎችን ለመደበቅ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ” ያላቸውን አምስት ወጣቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ጠቁሟል። ተጠርጣሪዎቹ ወጣቶች የተያዙት ከአምስት የጦር መሣሪያዎች እና ከሁለት የእጅ ሬዲዮዎች ጋር እንደሆነም ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው አክሏል።
የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እያከናወነ የሚገኘውን “የህግ ማስከበር ስራ” አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። በክልሉ የተቋቋመው የጸጥታ ግብረ ኃይል ከትላንት በስቲያ ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ በጋምቤላ ከተማ “አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን” የፌዴራል እና የጋምቤላ ክልል የጸጥታ አካላት “በቅንጅት እየሰሩ” መሆኑን ገልጾ ነበር።

ግብረ ኃይሉ በዚሁ መግለጫው በጋምቤላ ከተማ ያለው የሰላም ሁኔታ እና የአገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱን በመጥቀስ፤ ህብረተሰቡ “በፍርሃትና በስጋት ሳይገደብ” የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል። በጋምቤላ ከተማ ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ፤ የከተማዋ መደበኛ እንቅስቃሴ ለቀናት ተቋርጦ ቆይቷል።
በጋምቤላ ከተማ ያለውን የጸጥታ ችግር “እንደ አጋጣሚ በመጠቀም”፤ የዝርፊያ ሙከራዎች ሲደረጉ እንደነበርም የጸጥታ ግብረ ኃይሉ ጭምር አረጋግጧል። በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የተወሰኑ የከተማይቱ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሄዳቸውንም ያመነው ግብረ ኃይሉ፤ እነዚህን ነዋሪዎች ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































