የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በስምንት አመት ለአምስተኛ ጊዜ አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተሾመለት 

ከሁለት ሳምንት በፊት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር በመሆን በተሾሙት በቀድሞው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍስሃ ይታገሱ ምትክ፤ የእርሳቸው ምክትል የነበሩት አቶ ፍጹም ከተማ መስሪያ ቤቱን እንዲመሩ ተሾሙ። ለኮርፖሬሽኑ አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲሾም፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ አስተዳደር እና አመራርን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት የተጣለበት ይህ ኮርፖሬሽን የተመሰረተው በ2006 ዓ.ም ነው። ከመንግስት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኮርፖሬሽኑ፤ በስሩ 14 ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ያስተዳድራል።

በኮርፖሬሽኑ ከ10 ዓመታት በላይ በተለያዩ የአመራርና የኃላፊነት ቦታዎች ላገለገሉት አቶ ፍጹም፤ ከሐሙስ ጥቅምት 12፤ 2019 ጀምሮ ተቋሙን እንዲመሩ ሹመት የሰጧቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። አቶ ፍጹም ሹመቱን እስካገኙበት ዕለት ድረስ፤ በተቋሙ የፓርክ አስተዳደር እና ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። 

ፎቶ፦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 

አዲሱ ተሿሚ ወደዚህ የኃላፊነት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት፤ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ። አቶ ፍጹም በ2008 ዓ.ም ስራ የጀመረውን የሀዋሳ ልዩ ኢንዱስትሪ ፓርክንም ለአምስት ዓመት ከመንፈቅ በስራ አስኪያጅነት መርተዋል። 

ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት አቶ ፍጹም፤ በዚሁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በመምህርነት እና በትምህርት ክፍል ኃላፊነት ለስድስት ዓመት ገደማ አገልግለዋል። አቶ ፍጹም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከመጡ በኋላ ባለፈው አስር ዓመት ተቋሙን ከመሩ አምስት ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ጋር የመስራት ዕድል አግኝተዋል። 

ከሰኔ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስካለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ ኮርፖሬሽኑን ሲመሩ የቆዩት፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ዶ/ር ፍስሃ ይታገሱ ነበሩ። ከዶ/ር ፍስሃ በፊት ተቋሙን ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት፤ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አክሊሉ ታደሰ ናቸው። 

ፎቶ፦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 

ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቅርብ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ወጣት አመራሮች የሚሾሙበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን፤ አቶ ሳንዶካን ደበበም መርተውታል። አቶ ሳንዶካን ኮርፖሬሽኑን ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ከመሩ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የኢትዮጵያ ኒውክለር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው በተከታታይ ተሹመዋል።

ከእርሳቸው አስቀድሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ዶ/ር ለሊሴ ነሜ ናቸው። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር የተለያዩ መስሪያ ቤቶችን እንዲመሩ ከተሾሙ ወጣት ባለስልጣናት አንዷ የሆኑት ዶ/ር ለሊሴ፤ በአሁኑ ወቅት የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

We are hiring!