የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት የሀገሪቱን “ተጽዕኖ በዓለም ላይ ሊያሳይ በሚችል መልኩ” እንዲቃኝ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። “ፍላጎታችን ኢትዮጵያ በዓለም እንድትለወጥ ሳይሆን፤ ራሷም ገዝፋ ዓለምን እንድትለውጥ ማድረግ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
አብይ ይህን ያሉት ዛሬ ሰኞ መስከረም 25፤ 2019፤ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት ላስቀጠለላቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር ነው። ሃምሳ ደቂቃ ገደማ በወሰደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፤ ዓለም አቀፋዊ እና ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል።
ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁኔታዎች የደረሰባትን ተጽዕኖ፣ አሁን ያለችበትን ቦታ እንዲሁም ወደፊት የሚጠብቃት እድል እና የሚያጋጥማት ተግዳሮት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በሰፊው ተዳስሷል። የሀገሪቱ “ስልጣኔ” ያለ እሱ “እውን ሊሆን አይችልም” የተባለለት፤ የባህር በር የማግኘት ጉዳይም በንግግሩ ተነስቷል።
“ዛሬ ዘመኑ ተቀይሯል። ነገሮች እንደድሮው አይደሉም። ሃገራዊ፣ ቀጠናዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች በፍጥነት ይለዋወጣሉ” ያሉት አብይ፤ ዓለም “በጂኦ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች” ምክንያት “መልክ እና ጠባይዋ” መቀያየሩን አስረድተዋል። በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታ “ቋሚ አስተላለፍ ማየት ብርቅ መሆኑን” የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አይገመቴነት የዘመኑ ዋነኛ መገለጫ እየሆነ ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ የዘመኑን አካሄድ፤ ራሳቸው ላነሱት ጥያቄ ምላሽ እየሰጡ አብራርተዋል። “የባለዙ አለም ዋልታ ሊወለድ በሚታገልበት በዚህ ወቅት፤ ጎራ መርጦ ማን ይቆማል? ማንም። የትኛው ፖለቲካዊ እሳቤ በዓለም ላይ እንደሚነግስ ከግምት በዘለለ በርግጠኝነት ማን መናገር ይችላል? ማንም። ምን አይነት የኢኮኖሚ አካሄድ የቀጣይ ዓለም ስርዓት እንደሚሆንስ በውል ተለይቷልን? በፍጹም” ያሉት አብይ፤ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አውድ “ጥቁርና ነጩ ያለየለት ግራጫ” አካሄድ መሆኑን በንግግራቸው አትተዋል።
“ታሪክ ወደ የትኛው አዲስ ምዕራፍ እንደሚያደርሰን በግልጽ በማይታወቅበት መንታ መንገድ ላይ መሆናችን እሙን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ለዚህ ወቅት ዝግጁ የመሆኗን ጉዳይ በንግግራቸው አጠይቀዋል። “ዛሬስ ኢትዮጵያ ምን ያህል ተዘጋጅታለች? ካለፉት ስህተቶቻን ምን ያህል ተምረናል? አንዳችን የሌላችንን እንከን መንቀስ ትተን፤ አይናችን ምን ያህል ወደ ውጭ ያማትራል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
“ከትላንት በስቲያ በምድር ያገኘነው ባላንጣ፤ ትላንት በሰማይ ሲመጣ የተገረምን ህዝቦች፤ ነገ ጠላት ቤት በኩል ሊጎበኘን እንደሚችል አስበን እና ገምተን ምን ያህል ዝግጁ ሆነናል?”
“ከትላንት በስቲያ በምድር ያገኘነው ባላንጣ፤ ትላንት በሰማይ ሲመጣ የተገረምን ህዝቦች፤ ነገ ጠላት ቤት በኩል ሊጎበኘን እንደሚችል አስበን እና ገምተን ምን ያህል ዝግጁ ሆነናል?” ሲሉም ተጨማሪ ጥያቄ አክለዋል። ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና “እየተቀየረ” መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች፣ የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባህር ከባቢ “በለውጥ ማዕበል እየተጎበኘ” መሆኑን በንግግራቸው አመልክተዋል።
“ምስራቅ አፍሪካ፣ ቀይ ባህር እና የህንድ ውቅያኖስ በሚገናኙበት ልዩ ስፍራ ላይ መቀመጥ፤ ፈተናም እድልም አለው። የዓለም የነዳጅ ምርት መተላለፊያ የሆነው ባብ-ኤል መንደብ በእኛ ቀጠና መገኘት አንድምታው ብዙ ነው” ያሉት አብይ፤ ይህንን ለመገንዘብ “ብዙ ማሰላሰል” እንደማይጠይቅ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
“በእዚህ ቀጠና የሚነሳ የለውጥ ዝናብ፤ እኛን ሳያገኘን ያልፋል ማለት ዘበት ነው። ፈለግንም፣ አልፈለግንም፤ የእዚህ ከባቢ ለውጥ እኛንም ይጎበኘናል። ለዚህም ታሪክ ምስክር ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል። ቀጠናው ከጥንት ጀምሮ የየወቅቱ “ሃያላን መራኮቻ” እንደነበር የጠቀሱት አብይ፤ የእነዚህ ሁኔታዎች “ዕዳ እና ምንዳ” ለኢትዮጵያም እንደተረፋት ታሪክን አጣቅሰው አስረድተዋል።

“የሃያላኑ ሽኩቻ በተደጋጋሚ ቀጠናውን ቀይሮታል። የሀገራችንንም ቅርጽ ወስኖታል። ነጻነታችንን ለማስከበር ስንል ትኩረታችን ከልማት ወደ ጦርነት እንዲዞር አድርጎታል። የባህር በር ተጋሪነታችን የተለወጠው፣ የተጽዕኖ አድማሳችን ሲኮሰምን የኖረው፤ ፈልገን ብቻ አይደለም። ተገድደን ጭምር ነው” ሲሉም የጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ላይ ያስከተሏቸውን ችግሮች ዘርዝረዋል።
“አቅም በነበረን ወቅት የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን ወስነናል። በተዳከምን ጊዜ ግን ሌሎች በእኛ ላይ ወስነውብናል። በተዘጋጀንባቸው ዘመናት፣ ከቀይ ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ፣ ከሜዲትራንያን እስከ አትላንቲክ ተጉዘናል። ባልተዘጋጀንበት ወቅት ደግሞ መውጫ መግቢያ በራችን ተዘግቶብናል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ኢትዮጵያ የተዘጋባት “የባህር በር” እንዲኖራት ተግተው እንደሚሰሩ ለፓርላማ አባላቱ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ይህንን እውን ለማድረግ ከጎረቤት ሀገራት ጋር “የሰጥቶ መቀበል መርህ” እንደሚከተሉ አስረድተዋል። “ጎረቤቶቻችን በተፈጥሮ ያገኘናቸው ወዳጆቻችን ናቸው። በመሆኑም ከሁሉም ጎረቤቶች ጋር በሰላም በጋራ ጥቅም እና በትብብር የመስራት መርሃችን እንገፋበታለን” ሲሉም ተደምጠዋል።

ከጎረቤት ሀገራት በተጨማሪ ከሁሉም የአለም አካላት ጋር የኢትዮጵያን “ብሔራዊ ጥቅም መሰረት” ባደረገ አኳኋን አብረው እንደሚሰሩም አብይ በንግግራቸው ጠቁመዋል። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣዩቹ አምስት ዓመታት የሚከተሉት አቅጣጫ ምን ሊሆን እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል።
አብይ ይህን ጥቆማ የሰጡት፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት የሀገሪቱን “ተጽዕኖ በአለም ላይ ሊያሳይ በሚችል መልኩ እንዲቃኝ እንደሚደረግ” በገለጹበት የንግግራቸው ክፍል ነው። “እኛ ወደ አለም ስንገባ፤ ትልቋ ኢትዮጵያ ትንሽ እንድትሆን አንፈልግም። ማንነቷን ያጣች ሃገር እንድትሆን አንሻም። ፍላጎታችን ኢትዮጵያ በአለም እንድትለወጥ ሳይሆን፤ ራሷም ገዝፋ አለምን እንድትለውጥ ማድረግ ነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋማቸውን አሳውቀዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ “anchor state” መሆኗን “በተግባር የማሳየት” ትልም እንዳላቸውም አብይ በንግግራቸው ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ“የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የዓለም እና የአካባቢያችንን ወቅታዊ ሁኔታ ብሎም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ሃይል እንዲኖረን እንሰራለን” ሲሉም ተደምጠዋል።
“በቀጠናችን የአየር የበላይነት ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ ትገነባለች። የሚኖረን መከላከያ ዘመናዊ፣ ፈጣሪ፣ ሁሌም ዝግጁ፣ ብቁ እና ንቁ በየአውዶቹ የመሰማራት አቅም እና ቁመና ያለው ይሆናል። ችግሮች ሳይፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ማወቅ እና መግታት፣ ከመጡም መከላከል፣ ከባሰም እንደ አባቶቹ፣ እንደ ልማዱ፤ ማሸነፍ የሚችል ኃይል ሆኖ ይገነባል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ቃል ገብተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































