የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ሶስተኛ ፕሮግራም፤ በመንግስት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የህዝብ ብዛት ትንበያዎች መካከል ባለው “ከፍተኛ ልዩነት” ሁለት የተለያዩ የዕቅድ አማራጮች ለማዘጋጀት ተገድዷል። የመስሪያ ቤቱ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ “ለሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ” ያለመ ነው።
በዘርፉ ዋና የመንግስት የፖሊሲ ሰነድ የሆነው ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም ይፋ የተደረገው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር። ሰነዱ የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች አንድ አካል የሆነውን እና በመላ አገሪቱ “አስተማማኝ፣ ዘመናዊ እና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ” ለማዳረስ የተያዘውን ዕቅድ ዳግም የከለሰ ነው።
ከዚህ ቀደም ስራ ላይ የነበረው ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ሁለተኛ ፕሮግራም፤ ዕቅዱን ለማሳካት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ከመጋቢት 2011 ዓ.ም. እስካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ድረስ ነበር። ዶ/ር ስለሺ በቀለ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሳሉ በመጋቢት 2011 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ይህ ዕቅድ፤ 65 በመቶ ኢትዮጵያውያንን ከብሔራዊ የኃይል ቋት፣ ቀሪውን 35 በመቶ ደግሞ ከሌሎች የኃይል ማመንጫዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የማድረግ ውጥን ነበረው።

ሁለተኛው ፕሮግራም በዚህ መልኩ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን በመላ አገሪቱ ለማዳረስ ቢወጥንም ሳይሳካ ቀርቷል። ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ፤ በኢትዮጵያ ካሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኤሌክትሪክ የሚያገኙት አንድ አራተኛው ብቻ ናቸው። በሀገሪቱ ካሉ ጤና ማዕከላት የኤሌክትሪክ አገልግሎትን የሚጠቀሙት አንድ ሶስተኛው ብቻ እንደሆኑ ይኸው መረጃ ያሳያል።
ከኢትዮጵያ ክልሎች “ውስን የኃይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማት” እና “ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ሽፋን ምጣኔ” ያለባቸው፤ አፋር፣ ሶማሌ፣ ደቡባዊ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ መሆናቸውን በብሔራዊ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ሶስተኛ ፕሮግራም ሰነድ ላይ ሰፍሯል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ የተደረገው የሶስተኛ ፕሮግራም ሰነድ፤ በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ “ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደሌላቸው” አሳይቷል። ይህ አሀዝ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ያከናወነው የዓለም ባንክ በሚያቀርባቸው መረጃዎች ላይም በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ነው።

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ (IEA) ዓመታዊ ሪፖርት በአንጻሩ፤ “ወደ 85 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች” በተቋሙ “መሰረታዊ አገልግሎት” ብያኔ ውስጥ የሚካተቱትን “የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች እንደማያገኙ” አመልክቷል። በተቋሙ “መሰረታዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት” ብያኔ ውስጥ የሚካተቱ ሰዎች፤ አምፖሎች ለማብራት፣ ስልክ ለመሙላት፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቭዥን እና ማቀዝቀዣ ለመጠቀም የሚያስችላቸው ኃይል የሚያገኙበት አቅርቦት ያላቸው ናቸው።
ይኸው የዓለም አቀፉ ተቋም ሪፖርት፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት በከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ከፍተኛ ልዩነት እንደሚታይበት አትቷል። ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የሚመሩት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሶስተኛ ፕሮግራም ሰነድ፤ 94 በመቶ የከተማ፤ 43 በመቶ የገጠር ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ እንደሆኑ ያሳያል።
በኢትዮጵያ ያሉ የኃይል ማስተላለፊያዎች አስተማማኝነት እና የአገልግሎት ጥራት “ደካማ” በመሆናቸው፤ የደንበኞችን ፍጆታ፣ የማምረቻዎች አጠቃቀም እና ሰፊውን ኢኮኖሚያዊ ልማት “የተገደበ እንዲሆን” ማድረጉን ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተማማኝ፣ በዋጋ ተመጣጣኝ እና ከፍተኛ ፍጆታን የሚደግፍ መሆኑን ማረጋገጥ፤ ለኢትዮጵያ “ዋናው ተግዳሮት” እንደሆነም ሪፖርቱ ይጠቁማል።

በኢትዮጵያ ኃይል በማመንጨት የሀገሪቱን ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነት በዋናነት የተጣለው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ላይ ነው። መስሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት ካመነጨው 35.7 ቴራዋት ሰዓት ኃይል ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የህዳሴ ግድብ ድርሻ ነው።
ይህ ድርሻ ከቀደመው ዓመት በ25 በመቶ እድገት አሳይቷል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከሚመነጨው ኤሌክትሪክ ውስጥ ውሃ 95 በመቶ፣ ንፋስ አምስት በመቶ ድርሻ አላቸው።
ሀገሪቱ ኃይል የማመንጨት አቅሟን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 9.7 ጊጋዋት፤ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ወደ 14 ጊጋዋት ገደማ ማሳደግ ትፈልጋለች። በግንባታ ላይ የሚገኘው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ዕቅዱን ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማስፋፋት ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማትን የሚመሩ ኃላፊዎች፤ የጸሀይ እና የከርሰ ምድር እንፋሎት የኃይል ምንጮችን ማስፋፋት ይፈልጋሉ። ግንባታው እስከ 10 ዓመት ሊወስድ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው የኒውክሌር የኃይል ማመንጫ፤ መንግስት አይኑን የጣለበት ሌላ አማራጭ ነው።
ሆኖም የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለደንበኞች ለማዳረስ፤ በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች ያለው የህዝብ አሰፋፈር ትልቁ ፈተና ይመስላል። ከብሔራዊ ቋት ወደ ገጠራማ አካባቢዎች የኃይል ማስተላለፊያዎች መዘርጋት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ፤ ከጸሀይ ኃይል የሚያመነጩትን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶታል።
በሚቀጥሉት ዘጠኝ ዓመታት በመላ ሀገሪቱ ኤሌክትሪክ ለማዳረስ የተዘጋጀው ፖሊሲ፤ የህዝብ ቁጥርን በተመለከተ ባለው የተለያየ ትንበያ ምክንያት ሁለት አማራጭ ዕቅዶች ቀርቦበታል። የትንበያው ልዩነት “በኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታ ዕቅድ ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ” እንደሚያሳድር የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ሶስተኛ ፕሮግራም ሰነድ ያብራራል።

በዚህም ምክያት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሁለት የተለያዩ የዕቅድ አማራጮች ለማዘጋጀት ተገድዷል። የመጀመሪያው “የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 133 ሚሊዮን ይሆናል” የሚለውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትንበያ መሰረት ያደረገ ነው።
ሁለተኛው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ትንበያ በ22 ሚሊዮን ዝቅ በሚለው፤ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ ላይ የተመረኮዘ ነው። በመስሪያ ቤቱ ትንበያ መሰረት እስከ ፈረንጆቹ 2024 አቆጣጠር ድረስ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 111 ሚሊዮን ነው።
የህዝብ እና የቤት ቆጠራ ከታቀደለት ጊዜ አስር ዓመታት ገደማ በመዘግየቱ፤ መንግስት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ የስነ-ህዝብ መረጃ ማሰባሰቢያ ስልቶች እና ግምቶች ላይ ይመረኮዛሉ። በዚህ ምክንያት የተፈጠረው የትንበያ ልዩነት፤ በመላ ሀገሪቱ ኤሌክትሪክ ለማዳረስ የተዘጋጁት ሁለት የዕቅድ አማራጮች የሚያስፈልጋቸው የገንዘብ መጠንም የተለያየ እንዲሆን አድርጎታል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ፕሮግራም በመጀመሪያው የዕቅድ አማራጭ፤ በመጪዎቹ ዘጠኝ ገደማ ዓመታት በመላ አገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማዳረስ መንግስት 18 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ያሳያል። ለሁለተኛው የዕቅድ አማራጭ የሚያስፈልገው ገንዘብ በአንጻሩ 12.9 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው።
በመጀመሪያው አማራጭ በብሔራዊ የኃይል ቋት ላይ ለሚከናወኑ ስራዎች 16.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሎ ታቅዷል። ለተመሳሳይ ስራ ለሁለተኛው አማራጭ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 11.2 ቢሊዮን ዶላር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































