በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ዋጋ ግሽበት “በድርብ አሃዝ” ውስጥ ይቆያል ተብሎ እንደሚጠበቅ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ 

የዋጋ ግሽበት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት “በድርብ አሃዝ” ውስጥ ይቆያል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ። በመስከረም 2019 የተመዘገበው 14.9 በመቶ የዋጋ ግሽበት ከማዕከላዊው ባንክ የነጠላ አሃዝ ግብ “ከፍ ያለ” እንደሆነም አስታውቋል።

ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ አሃዞችን ይፋ ያደረገው፤ ሁለት ገለልተኛ ባለሙያዎችን ጨምሮ ስምንት አባላት ያሉት የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ካደረገው ስብሰባ በኋላ ነው። ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 24፤ 2019 የተካሄደው የኮሚቴው ስብሰባ፤ የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ የሀገሪቱን ዕድገት እና በጀት የተመለከቱ ጉዳዮች የተገመገሙበት እንደሆነ ተገልጿል።

በመስከረም ወር የተመዘገበው የምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት 14.9 በመቶ ሲሆን፤ ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ደግሞ 15.1 በመቶ ሆኗል። ለምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት ዕድገት “ከፍተኛ አስተዋጽኦ” አድርገዋል በሚል በብሔራዊ ባንክ የተጠቀሰው፤ የዳቦ፣ የእህል፣ የአትክልት የጥራጥሬ ምርቶች እና የቡና ዋጋ መጨመር ነው።

የኤሌክትሪክ ታሪፍ፣ የኬሮሲን እና የማገዶ እንጨት ዋጋ መጨመር፤ ምግብ ነክ ላልሆኑ ዕቃዎች የዋጋ ግሽበት ዕድገት ምክንያት ተብለው በማዕከላዊው ባንክ የተዘረዘሩ ናቸው። ባለፈው መስከረም ወር ለታየው የዋጋ ግሽበት ዋነኛው ምክንያት፤ “ከአቅርቦት ጋር የተያያዘ” እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ውጤት ያሳያል።

ችግሩ በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትን ተከትሎ የተፈጠረ እንደሆነ በኮሚቴው ድምዳሜ ላይ እንደተደረሰ ብሔራዊ ባንክ ከስብሰባው በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ ሰፍሯል። የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት “እየቀነሰ ይሄዳል” የሚል ትንበያ ቢኖረውም፤ ግሽበቱ ግን “በድርብ አሃዝ ውስጥ እንደሚቆይ” አስታውቋል።

ባደጉት አገራት ማዕከላዊ ባንኮች የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ ባንኮች በሚሰጡት ብድር ላይ የሚከፈለውን ወለድ ዝቅ ለማድረግ እና የሚገመት የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማበረታታት የዋጋ ግሽበትን በሁለት በመቶ ገደማ እንዲሆን ለማድረግ ይጥራሉ። በኢትዮጵያ ይህ ኃላፊነት የተጣለበት ብሔራዊው ባንክ ከ30 በመቶ በላይ አሻቅቦ የነበረውን ግሽበት በነጠላ አሃዝ ለመገደብ ያስችላሉ ያላቸውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲዎች እንደሚከተል ያሳወቀው በሰኔ 2016 ዓ.ም ነበር።

በታህሳስ 2018 ግሽበቱ ወደ 9.7 በመቶ ዝቅ ብሎ የነበረ ቢሆንም የኢራን ጦርነት ባስከተለው የነዳጅ እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ተመልሶ አሻቅቧል። በተያዘው 2019 የበጀት ዓመት የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሃዝ እንዲወርድ እንደሚደረግ ፕሬዝደንት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የመንግስትን ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተ ባደረጉት ንግግር አስታውቀው ነበር።

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው በዛሬው ስብሰባው፤ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሚከተለው የገንዘብ ፖሊሲ “መጠነኛ ልልነት” እንደታየበት መገምገሙን የባንኩ ገዢ የሆኑት ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ይህ በቀጥታ ብሔራዊ ባንክ በሚያካሄደው የወርቅ ግዢ ወደ ገበያው ከሚገባው ጥሬ ገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው።

“ማዕከላዊ ባንኩ ወርቅ በመግዛቱ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ብር ወደ ንግድ ባንኮች የሄደ ቢሆንም… በስፋት ኢኮኖሚው ውስጥ አልተሰራጨም” ሲሉ ዶ/ር እዮብ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። ይሁንና ገንዘቡ “ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ እንዳይገባ አስፈላጊውን ነገር” ለማድረግ ኮሚቴው ውሳኔ እንዳሳለፈ የብሔራዊ ባንክ ገዢው አብራርተዋል።

በዚህም በወርቅ ግዢ ወደ ገበያው የተሰራጨውን ጥሬ ገንዘብ፤ ብሔራዊ ባንክ መልሶ የሚሰበስብበትን የውጭ ምንዛሬ ጨረታ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ዶ/ር እዮብ ባንኩ በገበያው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ጥሬ ገንዘብ ለመቆጣጠር የሚጠቀምበትን “የኦፕን ማርኬት ኦፐሬሽን” “አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ የዋጋ ግሽበት መቆጣጠሪያ ዋና ፖሊሲ፤ በብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ ላይ የሚመሰረት ነው። የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው “እየታየ ባለው መጠነኛ ልቅ የገንዘብ እና የፋይናንስ ሁኔታ” እንደዚሁም “ባለ ሁለት አሃዝ ሆኖ የሚቆየውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር”፤ ብሔራዊ ባንክ ሲከተል የቆየውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ “ማስቀጠል እንዳለበት” ውሳኔ አስተላልፏል። 

በዚህም መሰረት የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ፤ አሁን ባለበት 16 በመቶ ሆኖ ይቀጥላል። የብድር ዕድገት ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ ከተነሳ በኋላ፤ ባንኩ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ከባንኮች የሚጠይቀው መደበኛ የመጠባበቂያ ተቀማጭም ባለበት የሚቀጥል ይሆናል።

ይሁንና “የብድር ዕድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር” ከሆነ፤ ብሔራዊ ባንክ በሚያደርገው መደበኛ ግምገማ የእያንዳንዱን ባንክ የብድር እና የተቀማጭ ሂሳብ ጥምርታ ላይ በመመርኮዝ የተለየ “የመጠባበቂያ ተቀማጭ” የሚጠይቅበትን አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን እንደሚቀጥል ተገልጿል። 

ማዕከላዊው ባንክ “በኢኮኖሚው ውስጥ ከሚጠበቀው በላይ ትርፍ ገንዘብ ሲኖር” የጨረታ ሰነድ ለባንኮች በጨረታ በማቅረብ ገንዘብ የሚሰበስብበትን ግብይትም “አጠናክሮ እንደሚቀጥል” ዛሬ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።

ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ በብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ የወርቅ ግዢ ምክንያት ወደ ገበያ የሚገባው ገንዘብ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ነው። በወርቅ ግዢ ምክንያት የውጪ ምንዛሬ ክምችት እና ወደ ባንኮች የገባው ጥሬ ገንዘብ መጨመራቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። ጥሬ ገንዘብ ወደ ገበያው በማስገባት በዋጋ ግሽበት ላይ ጫና ከሚያሳድረው የወርቅ ግዢ ብሔራዊ ባንክ እንዲወጣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ግፊት እያደረገ ይገኛል። 

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም ዶ/ር እዮብ የሚመሩት ማዕከላዊ ባንክ፤ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ዓላማውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በወርቅ ግብይት ውስጥ ከሚያደርገው ተሳትፎ የሚወጣበትን የረጅም ጊዜ ዕቅድ እስከ መጪው ታህሳስ ወር መጨረሻ እንደሚያዘጋጅ አስታውቆ ነበር።

ይሁንና የብሔራዊው ባንክ ገዢ ጉዳዩ “ገና በጥናት ደረጃ” ላይ እንደሚገኝ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ዶ/ር እዮብ ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ግብይት የሚወጣበትን ሂደት “ጊዜ ወስደን በደንብ የምናጠናው ጉዳይ ነው” ቢሉም “በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቀየር አይመስለኝም” ሲሉ ተደምጠዋል። 

በወርቅ ገበያ “የግል ባንኮች እንዲሳተፉ ነው የምንፈልገው። በእኛ በኩል ምንም ችግር የለብንም” ሲሉ ዶክተር እዮብ ተናግረዋል። ካለፈው ዓመት የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ፤ ከፍተኛ ገቢ የተገኘው ከወርቅ ሽያጭ እንደነበር ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

We are hiring!