በሃሚድ አወል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ማክሰኞ መጋቢት 19፤ 2015 በሚኖረው መደበኛ ስብሰባው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎችን የሚሰጡትን ምላሽ እና ማብራሪያ እንደሚያዳምጥ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የፓርላማ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ያስገቡት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2008 ዓ.ም የወጣው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓመት ሶስት ጊዜ በፓርላማ እንደሚቀርቡ አስፍሯል። በተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ዓመታዊ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት የፌደራል መንግስትን ዕቅድ ካቀረቡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ በመገኘት የሚያደርጉት ገለጻ፤ በዓመቱ ከሚጠበቅባቸው የመጀመሪያው ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስትን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርቶች ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም በደንቡ ላይ ተቀምጧል። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ “መቅረብ የሚገባው ጉዳይ አለ” ብለው ካመኑ፤ በማንኛውም ጊዜ ለፓርላማው ሪፖርት ማቅረብ እንደሚችሉ በደንቡ ተፈቅዷል።
በዚህ አሰራር መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት፤ የዓመቱን የመጀመሪያ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ባለፈው ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። በነገው ዕለት ለሚካሄደው ተመሳሳይ ስብሰባ፤ የፓርላማ አባላት ጥያቄዎቻቸውን “በአስቸኳይ” እንዲያቀርቡ የተደረገው ከሳምንት በፊት እንደሆነ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች አመልክተዋል።
ከአንድ ወር ዕረፍት በኋላ የተመለሱት እነኚሁ የፓርላማ አባላት፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 9፤ 2015 በተወካዮች ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በነበራቸው ስልጠና ይኸው እንደተነገራቸው ምንጮቹ ገልጸዋል። ይህንኑ ያረጋገጡት አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፓርላማ አባል፤ “ ‘በአስቸኳይ አስገቡ’ ብለው ባለፈው ቅዳሜ ነገሩን። ቀን ላይ ነግረውን፤ ‘እስከ ማታ ድረስ’ አሉን” ሲሉ ለጥያቄ ማቅረቢያ የተሰጠው አጭር ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።
የፓርላማ አባሉ አክለውም፤ “ብዙዎቻችን ‘አይሆንም፤ ተረጋግተን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርብ አይነት ጥያቄ በአግባቡ ማዘጋጀት አለብን’ ስንል እስከ እሁድ አመሻሽ ድረስ አቅርቡ ተባለ” ሲሉ ጥያቄ የማቅረቢያ ጊዜው በአንድ ቀን እንዲራዘም መደረጉን አስረድተዋል። በዚህ አካሄድ እስከ ባለፈው ሳምንት እሁድ አመሻሽ ድረስ፤ የፓርላማ አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች አስገብተው ማጠናቀቃቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
የጥያቄ ማቅረቢያ ጊዜው ካበቃ በኋላ ያዘጋጁትን ጥያቄ ለማቅረብ የሄዱ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ጥያቄ ማስገባት አለመቻላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከእነዚህ የፓርላማ አባላት መካከል አንዱ፤ “አርፍጄ ሰኞ ጠዋት ላስገባ ስሄድ፤ already ጥያቄዎች ተመርጠው አልቀዋል። ለእርሳቸው ተልኳል አሉኝ” ሲሉ የዛሬ ሳምንት ሰኞ ረፋድ ጥያቄ ለማስገባት ሞክረው ያገኙትን ምላሽ አስረድተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ “ማንኛውም የቃል መልስ የሚፈልግ ጥያቄ የሚያቀርብ አባል፤ ጥያቄውን ቢያንስ ከአስር ቀን በፊት ለአፈ ጉባኤው በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት” ሲል ይደነግጋል። አፈ ጉባኤው በምክር ቤት አባላት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች መርምረው ሊቀበሉት ወይም ውድቅ ሊያደርጉት እንደሚችሉም ያትታል።
ጥያቄዎቹ ለአፈ ጉባኤው ከቀረቡ በኋላ፤ አፈ ጉባኤው በፓርላማው የመንግስት ዋና ተጠሪ ከሆኑት ግለሰብ ጋር በመሆን ጥያቄዎችን የመለየት ስራዎችን እንደሚያከናውኑ አንድ የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ጥያቄዎች በዚህ መልኩ ከተለዩ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚቀርቡም እኚሁ አመራር አክለዋል።
በነገው ዕለት በሚካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል፤ “የኑሮ ውድነትን የተመለከቱ ይኖራሉ” ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ጠቁመዋል። “ወደ አዲስ አበባ አትገቡም እየተባለ ወደ አማራ ክልል የሚመለሱ ሰዎች” ጉዳይን የተመለከቱ ጥያቄዎችም፤ በነገው የፓርላማ ስብሰባ ጥያቄ ሊቀርብ እንደሚችል ምንጮች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የፓርላማ አባላቱ ጥያቄዎቻቸውን ካስገቡ በኋላ በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት “ልዩ ጉባኤ”፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብርተኝነት ለመሰረዝ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ 61 የተቃውሞ ድምጽ እንደገጠመው ይታወሳል። ይህንኑ የውሳኔ ሃሳብ ከተቃወሙት በተጨማሪ አምስት የፓርላማ አባላትም ድምጽ ተዐቅቦ አድርገዋል። በአብላጫ ድምጽ የጸደቀውን፤ ህወሓትን ከሽብርተኝነት ድርጅት የሰረዘውን የውሳኔ ሃሳብ በተመለከተ በነገው ስብሰባ ላይ የሚነሳ ጥያቄ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለነገው መደበኛ ስብሰባ እስከ ትላንት አመሻሽ ድረስ ጥሪ እንዳልደረሳቸው፤ አራት የፓርላማ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ለአፈ ጉባኤው ያቀረቡት ጥያቄ የተመረጠላቸው የፓርላማ አባላት፤ ስብሰባው ከመካሄዱ 48 ሰዓታት በፊት በስልክ ተደውሎ ይነገራቸው እንደነበርም አስታውሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)