የአማራ ክልል የሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጀመረ 

በተስፋለም ወልደየስ

በመጪው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከአማራ ክልል የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደት፤ ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 27፤ 2017  በባህርዳር ከተማ በይፋ ተጀመረ። የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው በባህርዳር ከተማ የተሰባሰቡ ከ4,500 በላይ ተሳታፊዎች፤ ክልሉን በመወከል በሀገር አቀፉ ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን ይመርጣሉ።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስቴዲየም በተካሄደው በዛሬው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የማህበረሰብ ክፍሎቹ ተወካዮች፤ የምክክር ሂደቱን በታማኝነት ለመፈጸም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። በአማራ ክልል ካሉ 263 ወረዳዎች የተውጣጡት እነዚህ ተወካዮች፤ በቀጣዩቹ አራት ቀናት የክልሉን አጀንዳዎች ለመለየት ምክክሮችን ያካሄዳሉ።

ተወካዮቹ ምክክራቸውን የሚያካሄዱት በሶስት ቡድኖች ተከፋፍለው ነው። የመጀመሪያው ቡድን የምዕራብ፣ ምስራቅ እና ሰሜን ጎጃም ዞኖችን፣ የባህርዳር እና ደብረ ማርቆስ ከተሞችን እንዲሁም የሰሜን ሸዋ ዞን ተወካዮችን የያዘ ነው። 

ሁለተኛው ቡድን የማዕከላዊ፣ ደቡብ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖችን፣ የጎንደር እና ደብረታቦር ከተሞችን፣ አዊ ብሔረሰብ ዞን እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ ስቲት ሁመራ አካባቢ ተወካዮች የተካተቱበት ነው። በሶስተኛ ቡድን ያሉ ተወካዮች የደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች እንዲሁም የዋግ ኽምራ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ተወካዮች የሚገኙበት ነው። 

የማህበረሰብ ክፍል ወኪሎቹ ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ምክክር የአማራ ክልልን አጀንዳ የመለየት እና ማጠናቀርን እስከ ሚያዝያ 4 ቀን ድረስ ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዛሬው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ተወካዮቹ “በርካታ ውጣ ውረዶች እና ስጋቶችን በማለፍ” በባህርዳሩ የምክክር ሂደት ላይ በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

የመድረኩ ተሳታፊዎች በቀጣይ ቀናት በሚኖራቸው የምክክር ሂደት፤ በ“ኃላፊነት ስሜት” “የነቃ ተሳትፎ” እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ዋና ኮሚሽነሩ በዚሁ ንግግራቸው፤ በክልሉ ያሉ ታጣቂዎች በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ከዚህ ቀደም በነበሩ መድረኮች ያቀረቡትን ጥሪ በድጋሚ አስተጋብተዋል።

“የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደቱ ሁሉን አካታች እና አሳታፊ መሆን እንዳለበት በጽኑ ከማመን ባለፈ፤ ህጋዊ ግዴታው እንደሆነ በቅጡ ይገነዘባል። ለዚህም በክልሉ ያሉ ታጣቂ ወገኖቻችንን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች እንዲሳተፉ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። አሁንም ሁሉንም አሸናፊ ወደሚያደርገው የምክክር መድረክ ሁሉም ተሳታፊዎች [እንዲመጡ]፤ ኮሚሽኑ ለታጣቂዎች በድጋሚ ጥሪ ያቀርባል” ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል። 

ከእርሳቸው አስቀድመው ንግግር ያደረጉት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 11 ኮሚሽነሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ወልደማርያም፤ የሀገራዊ ምክክር የተጀመረው በኢትዮጵያ ለዘመናት የተስተዋለውን “የጦርነት እና እርስ በእርስ የመተላለቅ አዙሪት” “ለማስቆም ያስችላል” በሚል እንደሆነ አስታውሰዋል። ምክክር ለዚህ አይነት ችግሮች “የመጨረሻ ፍቱን መድኃኒት ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በዚህ ዘመን “ወሳኝ ጉዳይ” እንደሆነ አስገንዘበዋል።

“እርስ በእርስ መጨራረስ በቃ ልንል ይገባል። ከዚህ ቀን ጀምሮ በኢትዮጵያ በየትኛውም ግዛት የሰው ደም ማፍሰስ ማቆም አለበት። እናቶች የሚያለቅሱበት ዘመን ማብቃት አለበት። ወላጆች ልጅ አልባ የሚሆኑበት ዘመን ማብቃት አለበት። በመነጋገር አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ለማዋለድ እንችላለን” ብለዋል ኮሚሽነር መላኩ። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ከተሰጣቸው ዓላማዎች መካከል፤ የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች “መተማመን የሰፈነበት እና አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ እንዲከናወኑ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት” የሚለው አንዱ ነው። ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚያከናውነው የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎች የማሰባሰብ እና ወኪሎችን የመምረጥ ሂደት፤ በ10 ክልሎች፣ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች አጠናቅቋል።

በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ያለው የአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ወኪሎችን የመምረጥ ሂደት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው በመጪው ሳምንት ቅዳሜ ሚያዝያ 4፤ 2017 ዓ.ም ነው። እስካሁን ድረስ ምን አይነት የሀገራዊ ምክክር ሂደት ያልተካሄደበት ትግራይ ክልል ብቻ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)