በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው “ድንበር ተሻጋሪ ውጥረት”፤ በመላ ቀጠናው ላይ “ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል” አሜሪካ ስጋቷን ገለጸች። የአፍሪካ ቀንድ ሌላ ወታደራዊ ግጭት እና ሰብአዊ ቀውስ የመሸከም አቅም እንደሌለው የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳስቧል።
ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ትላንት ቅዳሜ መስከረም 23፤ 2019 ለሊት ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚቀሰቀስ ግጭት ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ ጥቅሞች ላይ ከሁለቱ ሀገራት ጋር የምታደርገውን ትብብር “አደጋ ላይ ሊጥል” እንደሚችል ጠቁሟል። በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት “ድንበር ተሻጋሪ” ሲል የጠራው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ፤ ሁለቱ ሀገራት የጎረቤቶቻቸውን “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት” እንዲያከብሩ አሳስቧል።
ሀገራቱ ከግጭት ራሳቸውን “በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያቅቡ” እና በ2010 ዓ.ም በተፈራረሙት የሰላም ማዕቀፍ መሰረት “ወደ ውይይት እና ትብብር እንዲመለሱም” ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። “በውይይት የሚገኝ ሰላም ለዘላቂ ደህንነት፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለብልጽግና ብቸኛው መንገድ” መሆኑን መስሪያ ቤቱ በመግለጫው አስገንዝቧል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “ታሪካዊ” የተባለለትን የሰላም እና የወዳጅነት ስምምነት የተፈራረሙት በሐምሌ 2010 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበር። ሁለቱ ሀገራት ዝርዝሩ እስካሁንም በግልጽ የማይታወቀውን ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት፤ ከአንድ ወር በኋላ በሳዑዲ አረቢያ፣ ጅዳ ከተማ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ግንኙነታቸው የተቀዛ ቀዘው እና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በመካከላቸው ውጥረት የሰፈነው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከሁለት ቀናት በፊት አቋርጠዋል። በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ውጊያ “የኤርትራ ወታደሮች ተሳትፈዋል” ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እየወነጀሉ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ባለልስጣናት አንዱ ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አብርሃም በላይ ናቸው። ዶ/ር አብርሃም ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ካለው ፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት እና ትላንት ቅዳሜ በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው “የሻዕቢያ ሰራዊት ከእነ ትጥቁ፣ ከእነ መሳሪያው” በጦርነቱ እንደተሳተፈ ተናግረዋል።

“የሞተም፣ የተማረኩ መሳሪያዎችም መዓት ናቸው” ያሉት ዶ/ር አብርሃም፤ ኢትዮጵያ የምትሰጠው ምላሽ “እጥፍ እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም” ሲሉ ተደምጠዋል። “ሰው ሀገር ገብቶ፤ ከሽፍታ እና ከባንዳ ጋር ሆኖ ተጣምሮ መምጣት ምን ሊያስከትል እንደሚችል በምላሹ ያገኘዋል” ሲሉም የኢትዮጵያ መንግስት ሊወስድ የሚችለውን እርምጃ ክብደት ጠቆም አድርገዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት በተባባሰበት በዚህ ወቅት፤ የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከግብጽ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር ትላንት ቅዳሜ መስከረም 23፤ 2019 ተገናኝተው ተወያይተዋል። ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የተገናኙት፤ በግብጿ የባህር ዳርቻ ከተማ አልአሚን እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ቢዝነስ ጉባኤ ጎን ነው።
ኢሳያስ እና አልሲሲ ባደረጉት ውይይት፤ ግብጽ ለኤርትራ ደህንነት እና መረጋጋት፤ እንዲሁም ሉዓላዊነቷ እና የግዛት አንድነቷ እንዲከበር ያላትን ቁርጠኝነት መግለጿን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የዓለም አቀፍ ህግጋትን እና የአፍሪካ ህብረት መስራች ድንጋጌ መርሆዎችን የሚጥሱ “ማናቸውንም የሀገራት ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መደፈሮች” ግብጽ አጥብቃ የምትቃወም መሆኗን አልሲሲ በዚሁ ውይይት ላይ መግለጻቸውን ጽህፈት ቤታቸው አክሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































