ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “መንገድ ስተው ከሀገራቸው በተቃራኒ የቆሙ” ላሏቸው ወገኖች፤ “ፊታቸውን ወደ ሰላም እንዲመልሱ” ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከዚህ በኋላ በጠብመንጃ አፈሙዝ እና ከጠላት ጋራ በመወገን የሚመለስ የኦሮሞ ጥያቄ ፈጽሞ አይኖርም” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
አብይ ይህን ያሉት፤ የኢሬቻ በዓልን በማስመልከት ዛሬ አርብ መስከረም 22፤ 2019 በጹሁፍ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው “ለዘመናት የቆየውን” የኢትዮጵያን “የፖለቲካ ባህርይ እና አስተዳደር” ከኢሬቻ በፊት ካለው የክረምት “አስቸጋሪ ወቅት” ጋር አመሳስለውታል።
“ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ሆና ሳለች የስሟን ያክል መሆን ሳትችል ቆይታለች” ሲሉ በመልዕክታቸው ላይ ያሰፈሩት አብይ፤ የእዚህ ምክንያቱ ሀገሪቱ “በዕውቀት እና በስርዓት አለመመራቷ” እንደሆነ አመልክተዋል። “[ኢትዮጵያ] የረጅም ዘመናት ሀገረ መንግስትነት ቢኖራትም፤ የህዝብን ችግር የሚፈታና ሀገርን የሚያሻግር ዘመናዊ አስተዳደር ለመገንባት ግን ስትቸገር ቆይታለች” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ “በትግሉ ያመጣው” ያሉትን “ለውጥ” የክረምቱ ጊዜ ካለፈ በኋላ ከሚመጣው “ብራ” ጋር ያነጻጸሩት አብይ፤ የሚመሩት መንግስት ለሀገሪቱ “የሰነቀውን የብራ ራዕይ” በጹሁፋቸው አስረድተዋል። ራዕዩ “በጠንካራ አንድነት ላይ የተመሰረተች፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረ እና ማንኛውንም ዓይነት ፈተና የምትቋቋም” ሀገር መገንባት መሆኑንም አመልክተዋል።
“ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ የማሻገር ስትራቴጂያዊ እቅድ በተግባር ላይ እየዋለ ነው” ሲሉ በመልዕክታቸው ላይ ያሰፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ለኢትዮጵያ መውጣት የጀመረው የለውጥ ብርሃን በየትኛውም የክረምት ጨለማ፣ ዶፍ እና ጭቃ ተንሸራትቶ ሊደናቀፍ አይችልም” ሲሉም ጠንከር ባሉ ቃላት መጪውን ጊዜ ገልጸዋል። በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት “ፈተናዎች” እንዳሉ በደፈናው የጠቆሙት አብይ፤ “እነዚህ ፈተናዎች ግን ከኢትዮጵያና ህዝቦቿ አቅም በታች ናቸው” ብለዋል።፡
“የአድዋ አባቶቻችንን ጀግንነት በማስቀጠል ኢትዮጵያን ከጠላት እየጠበቅን ነን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን የሚያደርጉት “ከባንዳ” ፊት ጭምር በመቆም እንደሆነ አብራርተዋል። አብይ “ጠላት እና ባንዳ” ሲሉ የጠሯቸው ኃይሎች፤ “እኔ ስጋ ብቻ ልብላ፤ እንስሳዬ ግን እንዳይነካ” የሚል አቋም የሚያራምዱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መንገድ ስተው ከሀገራቸው በተቃራኒ የቆሙ” ሲሉ ለጠሯቸው ወገኖችም የኦሮሞ ምሳሌያዊ አነጋገርን ተጠቅመዋል። እነዚህ ወገኖች “ፊታቸውን ወደ ሰላም እንዲመልሱ” ለማግባባት አብይ የጠቀሱት ምሳሌያዊ አነጋገር፤ “ከሚያመሹበት የሚያድሩበት ቤት ይሻላል” የሚል ነው።
አብይ በጹሁፋቸው በግልጽ ላልጠቀሷቸው ለእነዚህ ወገኖች፤ “የሰላም በር [አሁንም] እንደተከፈተ ያለ መሆኑን” ማረጋገጫ ሰጥተዋል። “ኦሮሞ በትግሉ ነጻ ወጥቷል። ከዚህ በኋላ በጠብመንጃ አፈሙዝ እና ከጠላት ጋራ በመወገን የሚመለስ የኦሮሞ ጥያቄ ፈጽሞ አይኖርም” ሲሉም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ወገኖች መልዕክት አስተላልፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































