ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መግባት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን የፍልሰት ጉዳዮች ለማስተናገድ፤ የአሜሪካ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚከፍተው ቢሮ በነገው ዕለት ስራ ሊጀምር ነው። በቢሮው ለመስተናገድ የሚሹ ኢትዮጵያውያን አስቀድመው ቀጠሮ መያዝ እንደሚጠበቅባቸው አገልግሎቱ ገልጿል።
መቀመጫውን በአዲስ አበባ የሚያደርገው አዲሱ ቢሮ ለቪዛ ማመልከቻዎች ውሳኔ የሚሰጥ እንዳልሆነ የአሜሪካ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት አስታውቋል። ሆኖም ቢሮው ኢትዮጵያውያን ለፍልሰት ማመልከቻዎቻቸው የሚያቀርቧቸውን ሰነዶች ትክክለኛነት የማረጋገጥ ስራን የሚያከናውን መሆኑን አገልግሎቱ አስገንዝቧል።
የተጠረጠሩ የሰነድ “ማጭበርበሮችን” የሚመረምሩት እና የቤተሰቦችን ዝምድና ለማረጋገጥ የዘረ-መል (DNA) ናሙናዎችን የሚሰበስቡት በአዲስ አበባ የሚከፈተው የአገልግሎቱ ቢሮ ሰራተኞች ይሆናሉ። እነዚህ ስራዎች ከዚህ ቀደም ሲከናወኑ የነበረው፤ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እንደነበር ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።

የአሜሪካ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት “ወሳኝ የስራ ኃላፊነቶች” ያላቸውን እነዚህን ተግባራት፤ አዲሱ ቢሮ “በቀጥታ ለማከናወን የሚያስችለውን ልዩ ውክልና ይሰጠዋል” ተብሏል። ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪ 11 ተመሳሳይ ቢሮዎች ያሉት አገልግሎቱ፤ በአዲስ አበባ የሚከፍተው ቢሮ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የሚገኘውን በመከተል በአፍሪካ ሁለተኛው ይሆናል።
በናይሮቢ የሚገኘው ቢሮ በዩናይትድ ስቴትስ ተገን የተሰጣቸው ግለሰቦችና ስደተኞች ዘመዶቻቸውን ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ማመልከቻዎች እየተቀበለ ያስተናግዳል። በአሜሪካ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ከአገሪቱ ወጥተው ተመልሶ የመግባት ፈቃድ ቢያስፈልጋቸው፤ በኬንያ ለሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ማመልከቻ የሚያቀርቡት በቢሮው በኩል ነው። ቢሮው ለመሰል ማመልከቻዎች ውሳኔ ባይሰጥም እያረጋገጠ ለኤምባሲው ያስተላልፋል።
ዩናይትድ ስቴትስ “ልዩ ውክልና” የሚሰጠውን ቢሮ በኢትዮጵያ ለመክፈት የወሰነችው፤ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ የቪዛ አገልግሎት በተመረጡ ቀጠናዊ ማዕከላት ብቻ እንዲከናወን ማድረጉን ተከትሎ ነው። ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው ውሳኔ፤ የአሜሪካ የቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ “ጥብቅ የደህንነት ፍተሻና ምርመራ መስፈርቶች” እንዲኖሩትና “ሃብቶችና የአሰራር አቅምን ከአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም እንዲጣጣም” የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።

በውሳኔው መሰረት በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚገኘውን ጨምሮ በ25 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ከነሐሴ 26፤ 2018 ጀምሮ የቪዛ አገልግሎት መስጠት አቋርጠዋል። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች በሆኑት በደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎችም መደበኛ የቪዛ አገልግሎት ማቋረጣቸው ይፋ ተደርጓል።
በአስመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍልሰት ውጪ ለሆኑ ለጉብኝት፣ ለስራ እና ለትምህርት ጉዞ ወደ አሜሪካ መግባት የሚሹ ኤርትራውያን የቪዛ ማመልከቻዎቻቸውን ማቅረብ የሚጠበቅባቸው በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ለሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ እንደሆነ አሳውቋል። ለፍልሰት ቪዛ የሚያመለክቱ ኤርትራውያንን የሚቀበለው በኬንያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































