በትግራይ ክልል በሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) መጋዝን ላይ ከትላንት በስቲያ እሁድ ዘረፋ መፈጸሙን የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ምክትል ቃል አቃባይ ገለጹ። በክልሉ ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ የዓለም አቀፍ እና ሀገር በቀል ድርጅቶች መጋዘኖች እና መገልገያዎች በተመሳሳይ መልኩ መዘረፋቸውንም ቃል አቃባዩ ተናግረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ምክትል ቃል አቃባይ ፋራህን ሃቅ ይህንን የተናገሩት፤ ትላንት ሰኞ መስከረም 25፤ 2019 ምሽት በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ኒውዮርክ በሚገኘው የተመድ ዋና ጽህፈት ቤት ከሰኞ እስከ አርብ ባሉት ቀናት የሚሰጠው ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አንገብጋቢ የሚባሉ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉዳዮች፣ የጂኦ ፖለቲካል ሁኔታዎች እና የሰብአዊ ቀውሶች የሚነሱበት ነው።
የዛሬ ሁለት ሳምንት በትግራይ ክልል እንዲሁም በአፋር እና አማራ ክልል አዋሳኝ ስፍራዎች ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ በእነዚህ ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ቀዳሚውን ቦታ ሲያገኝ ቆይቷል። በትላንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም፤ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተመሳሳይ ሁኔታ ተነስቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በቀጠለው የጸጥታ ችግር በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን የጠቆሙት የተመድ ዋና ጸሀፊ ምክትል ቃል አቃባይ፤ ይህ ሁኔታ የመንግስታቱ ድርጅትን “እጅግ እንደሚያሳስበው” አስታውቀዋል። ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በሰጠው መግለጫ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው “የድሮን እንቅስቃሴ እና የአየር ድብደባ”፤ በሲቪሎች ላይ “ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን” አስጠንቅቆ ነበር።
ተመድ በትላንትና መግለጫቸው በአጽንኦት ያነሳው ሌላው ጉዳይ፤ በትግራይ ክልል የራሱን ጨምሮ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መጋዘኖች ላይ “ተፈጽሟል” ያለውን ዘረፋ ነው። የእሁዱ ዘረፋ በትግራይ ክልል የትኛው አካባቢ እንደተፈጸመ እና በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያልጠቀሱት ምክትል ቃል አቃባይ ፋራህን፤ ሆኖም በክስተቱ የሰብአዊ አቅርቦቶች መጥፋታቸውን አስረድተዋል።
በዘረፋው ከተሰረቁት ውስጥ ምግብ፣ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያዎች እና የውሃ ፖምፖች እንደሚገኙበት የተመድ ዋና ጸሀፊ ምክትል ቃል አቃባይ ገልጸዋል። የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች፣ ተቋማት እና ንብረቶች “በፍጹም የጥቃት ኢላማ ሊሆኑ አይገባም” ያሉት ፋራሃን፤ በሁሉም ጊዜያት “ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ” ጨምረው አሳስበዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች መጋዘኖች ላይ ዘረፋ ሲፈጸም የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም። በነሐሴ 2013 ዓ.ም. በአማራ ክልል በኮምቦልቻ እና ደሴ በሚገኙ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) መጋዘኖች ላይ በወቅቱ ከተሞቹን በተቆጣጠሩት የትግራይ ክልል ኃይሎች እና በአካባቢው ነዋሪዎች ዘረፋ መፈጸሙ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።
በዚህ ክስተት በምግብ እጥረት ለተጠቁ ህጻናት የሚሰጥ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው መሰረታዊ የምግብ እርዳታዎችን መዘረፋቸውን የመንግስታቱ ድርጅት በወቅቱ አስታውቋል። ይህንን ዘረፋ ተከትሎ፤ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሁለቱ ከተሞች የሚያካሄደውን የምግብ ስርጭት ለተወሰኑ ጊዜ ማቋረጡም አይዘነጋም።
በተመሳሳይ መልኩ ንብረትነታቸው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) የሆኑ፤ በአማራ ክልል የሚገኙ መጋዘኖች “በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተዋጊዎች መዘረፋቸውን” ድርጅቱ በህዳር 2014 ዓ.ም ገልጾ ነበር። በወቅቱ በትግራይ ክልል የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የኤርትራ ኃይሎችም፤ “የድርጅቱን መጋዘኖች በመውረር እርዳታዎችን መዝረፋቸውን” በጊዜው በኢትዮጵያ የUSAID ኃላፊ የነበሩት ሳራ ጆንስ መናገራቸው ተዘግቧል።

ከትላንት በስቲያ በትግራይ ክልል የተከሰተውን የመጋዘን ዘረፋ እነማን እንደፈጸሙት፤ የተመድ ዋና ጸሀፊ ምክትል ቃል አቃባይ በሰኞ ምሽት መግለጫቸው ላይ አላብራሩም። የክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው መቐለ፤ ከአርብ ምሽት ጀምሮ በመንግስት እና የግል ተቋማት ላይ “ከፍተኛ ዝርፊያ” ሲፈጸም እንደነበር ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ዝርፊያው የተጀመረው የመቐለ ከተማን ጸጥታ ሲያስጠብቁ የቆዩ ኃይሎች፤ ከትላንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ ከተማይቱን ለቅቀው ከወጡ በኋላ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል። የጸጥታ ኃይሎቹ፤ ካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ወዲህ ትግራይ ክልልን የማስተዳደር ኃላፊነት ከጊዜያዊ አስተዳደር የወሰደው በህወሓት የሚታዘዙ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































