የቻይና ሁለት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በመጪዎቹ ሳምንታት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብጽን ሊጎበኙ ነው 

ቻይና የአፍሪካ ጉዳዮችን እንዲከታተሉ የመደበቻቸውን ሁለት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በመጪዎቹ ሳምንታት ወደ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብጽ እንደምትልክ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። “ሰላማዊ ውይይቶችን ለማበረታታት” እና “ውጥረቶችን ለማርገብ” የታለመ ነው በተባለለት በዚህ የቻይና ተልዕኮ፤ የሀገሪቱ ሶስተኛ ከፍተኛ ዲፕሎማትም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያቀናሉ።

የዲፕሎማቶቹ ጉዞ የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ “በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም እና ደህንነትን” ለማረጋገጥ እና “የአፍሪካን አሳሳቢ ጉዳዮች ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት ገንቢ ተሳትፎ እንዲያደርጉ” ያቀረቧቸውን አራት ምክረ ሀሳቦች እና መርሆዎች ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል። ይህ የተገለጸው ትላንት ሰኞ ጥቅምት 23፤ 2019 በቤጂንግ በተሰጠ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

የቻይናው ፕሬዝዳንት “በአፍሪካ አሳሳቢ” ያሏቸው ጉዳዮች ሊፈቱባቸው ይገባል ያሏቸውን አራት መርሆዎች ያስተዋወቁት፤ የዛሬ ሶስት ሳምንት ከቶጎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፋውሬ ኤሶዚምና ግናሲንግቤ ጋር በተገናኙበት ወቅት ነበር። ዢ ጂንፒንግ ካቀረቧቸው መርሆዎች መካከል በቀዳሚነት ያነሱት፤ በአህጉሩ የተፈጠሩ ቀውሶችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ “የአፍሪካን መሪነት ማስጠበቅ” ነው።

በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች “ፍትሃዊነትን እና እኩልነትን ማስከበር” የሚለው በቻይናው ፕሬዝዳንት የተነሳ ሁለተኛው መርህ ነው። “ግጭቶችን ማስቆም እና ሰላም ማስፈን” እንዲሁም ለግጭት “ምልክቶችን እና መንስኤዎች” መፍትሔ ማበጀት የሚሉት ቀሪዎቹ የፕሬዝዳንቱ መርሆዎች ናቸው።

የቻይናው ፕሬዝዳንት አራቱን መርሆዎች ይፋ ያደረጉት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ውጊያ ዓለም አቀፍ ትኩረት ባገኘበት ወቅት ነው። የፕሬዝዳንቱ ምክረ ሃሳቦች ከኢትዮጵያ የወቅቱ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው በጊዜው የተጠየቁት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ “መርሆዎቹ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሁኔታ ጨምሮ ችግሮችን ለመፍታት ተጨባጭ መመሪያ” ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረው ነበር።

ይህ በተገለጸ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፤ ቻይና የአፍሪካ ጉዳዮችን የሚከታተሉ ከፍተኛ ዲፕሎማቶቿን ውጥረት ወደተከሰተበት ቀጠና ለመላክ መዘጋጀቷን አስታውቃለች። በዚህ መሰረት የቻይና መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ልዑክ ሊዩ ዜየንፋ፤ በመጪዎቹ ሳምንታት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። 

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጅቡቲ እና ግብጽን የሚጎበኙት ሊዩ ዜየንፋ፤ የቻይና መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ልዑክ ሆነው የተሾሙት በጥር 2018 ዓ.ም. ነበር። የ63 ዓመቱ ዲፕሎማት ከአፍሪካ ሀገራት እና ከአፍሪካ ህብረት በሚደረገው ግንኙነት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን እንደሚወክሉ፤ መስሪያ ቤቱ ሹመታቸው ይፋ በተደረገበት ወቅት አስታውቆ ነበር።

ከዚህ ቀደም በኬንያ የቻይና አምባሳደር እና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የሰሩት ሊዩ ዜየንፋ፤ ስለ አፍሪካ ጉዳዮች ግንዛቤ ያላቸው ናቸው። የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ልዑኩ ወደ ሶስቱ ሀገራት በሚጓዙበት በተመሳሳይ ወቅት፤ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ ልዑክ ሁ ቻንግቹን ኤርትራን እንደሚጎበኙ ታውቋል።

የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ ልዑኩ ባለፈው ሚያዝያ ወደ አስመራ አቅንተው፤ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተወያይተዋል። ልዩ ልዑኩ ከኤርትራ ጉብኝታቸው በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርሃኑ ጸጋዬ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል።

 ቻይና ከሁለቱ ዲፕሎማቶች በተጨማሪ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ ልዑኳን በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ኢራን፣ ኦማን እና ሳዑዲ አረቢያ ትልካለች። ሶስቱ ዲፕሎማቶች ውጥረት ወደበረታባቸው ቀጠናዎች የሚያደርጉት ጉዞ ዓላማ፤ “ሰላማዊ ውይይቶችን ለማበረታታት” ያለመ እንደሆነ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ በትላንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

We are hiring!