ላለፉት 30 ዓመታት በህትመት ላይ የቆየው “ሪፖርተር” የአማርኛ ጋዜጣ “ላልተወሰነ ጊዜ” ከህትመት እና ከስርጭት “ሙሉ በሙሉ” ታገደ። በዚሁ መገናኛ ብዙሃን አሳታሚ ለህትመት የሚበቃው “ዘ ሪፖርተር” እንግሊዘኛ ጋዜጣ እና የጋዜጣው የበይነ መረብ ማሰራጫ ላይም ተመሳሳይ የእገዳ ውሳኔ ተላልፏል።
በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃ.የተ.የግል ማህበር በሚታተሙት ጋዜጦች እና በበየነ መረብ ማሰራጫ ላይ ውሳኔው ያስተላለፈው፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ነው። ባለስልጣኑ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 23፤ 2019 ባወጣው መግለጫ፤ የአሳታሚ ድርጅቱ የምዝገባ ምስክር ወረቀት “ላልተወሰነ ጊዜ” መታገዱን አስታውቋል።
መገናኛ ብዙሃን ተግባራቶቻቸውን በህግ መሰረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ “ክትትል እና ቁጥጥር” የማድረግ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ይህ ተቋም፤ በሪፖርተር አማርኛ እና እንግሊዘኛ ጋዜጦች እንዲሁም በዲጂታል ማሰራጫዎቹ በሚቀርቡ ይዘቶች ላይ “ከአንድ ዓመት በላይ ክትትል ሲያደርግ” መቆየቱን አስታውቋል። በዚህ ክትትልም፤ መገናኛ ብዙሃኑ “ተደጋጋሚ የህግ እና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶች መፈጸሙ ተረጋግጧል” ሲል መስሪያ ቤቱ ወንጅሏል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ “የህግ እና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶች” በሚል በዛሬ መግለጫው ላይ ከዘርዘራቸው ውስጥ “ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረሩ ይዘቶችን ማሰራጨት” የሚለው ይገኝበታል። መገናኛ ብዙሃኑ “የሀገር ገጽታን የሚያጠለሹ፣ የሀገርን ብሔራዊ ደህንነትን የሚጎዱ፣ የህዝቦችን አብሮነት እና እሴት የሚሸረሽሩ መረጃዎች አሰራጭቷል” ሲልም ባለስልጣኑ ከስሷል።
ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ እነዚህን ምክንያቶች በመጥቀስ መገናኛ ብዙሃንን ሲያግድ “ሪፖርተር” የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ዓመት ጥር እና የካቲት ወር በባለስልጣኑ የእግድ ውሳኔ የተላለፈባቸው “ዋዜማ” እና “አዲስ ስታንዳርድ” የተሰኙት የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንም ተመሳሳይ ምክንያት ተጠቅሶባቸዋል።
“ሪፖርተር”፣ “ዘ ሪፖርተር” እና የጋዜጦቹ የበይነ መረብ ማሰራጫዎች፤ “በሀገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በማንሳት ከሚሰጣቸው አርዕስት ጀምሮ የማጮህ (sensationalize)” አካሄድ በመከተልም በባለስልጣኑ ተወንጅለዋል። መገናኛ ብዙሃኑ “በተለያዩ መድረኮች እና ሪፖርቶች ላይ የሚገኙ ሀገራዊ መረጃዎችን አጠቃላይ አውዱን ተገንዝቦ መረጃን ከማድረስ ይልቅ፤ በቁንጽል እይታ ላይ ተመስርተው” ዘገባዎችን ያቀርባሉ የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል።
ባለስልጣኑ በዛሬው መግለጫው ያነሳው ሌላኛው የእግድ ምክንያት፤ በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም እና ዲፕሎማሲ ላይ “አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት” የሚለውን ነው። “ሚዛናዊነት የጎደለው አድሏዊ ዘገባዎችን ማሰራጨት”፣ “ከራስ ጥቅምና የግል ፍላጎት በመነሳት ባልተረጋገጠ መረጃ የተቋማትን ስምና ገጽታ ማጠልሸት” የሚሉትም ለእገዳው በምክንያትነት ከተዘረሩት ውስጥ ተካትተዋል።
መስሪያ ቤቱ የዘረዘራቸው “የህግ እና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶች” እንዲታረሙ፤ ከመገናኛ ብዙሃኑ ባለቤት እና ዋና አዘጋጆች ጋር “ተደጋጋሚ” ውይይት ማድረጉን በመግለጫው ጠቅሷል። ከውይይቶቹ በኋላም መገናኛ ብዙሃኑ “መታረም አለመቻሉን” የገለጸው ባለስልጣኑ፤ በዚህም ምክንያት “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሷል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የዛሬውን እግድ ያስተላለፈው፤ “ሪፖርተር” በሚያሰራጫቸው ይዘቶች ላይ “መሻሻሎች ባለመታየታቸው” መሆኑን አመልክቷል። በዚህ መሰረት የአሳታሚ ድርጅቱ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከዛሬ ጀምሮ “ላልተወሰነ ጊዜ” የታገደ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

እገዳው በመገናኛ ብዙሃኑ “የህግና የሙያ ስነ ምግባር ግዴታዎች ተሟልተው ተግባራዊ እስኪደረጉ ድረስ” የሚጸና እንደሆነ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ገልጿል። ይህ ተፈጻሚ እስኪሆን ድረስ “ሪፖርተር” እና “ዘ ሪፖርተር” የአማርኛ እና የእንግሊዝኛ ጋዜጦች እንዲሁም የበይነ መረብ ማሰራጫዎቹ፤ “ከህትመትና ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ታግዶ እንዲቆይ የተወሰነ መሆኑን” እና ይኸው ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ ባለስልጣኑ “ጥብቅ ማሳሳቢያ” ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































