ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በአፋር እና አማራ ክልል ባሉት አዋሳኝ አካባቢዎች ባሰማራቸው ታጣቂዎቹ፤ ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 12፤ 2019 ከለሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ “ጥቃት መክፈቱን” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ። በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና ህወሓት “ባሰማራቸው ታጣቂዎች” መካከል በዋግ ኸምራ ዞን አካባቢዎች እና በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ “ግጭቶች መከሰታቸውንም” ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኢሰመኮ ይህን ያስታወቀው በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ፤ ዛሬ አርብ መስከረም 15፤ 2019 ባወጣው መግለጫ ነው። በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በትግራይ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ስፍራዎች የነበረው “ውጥረት” “ከጊዜ ወደ ጊዜ” ሲባባስ መቆየቱን በመግለጫው ያስታወሰው ኮሚሽኑ፤ በእነዚህ አካባቢዎች “የትጥቅ ግጭቶች” “መቀስቀሳቸውን” ባሰባሰባቸው “መረጃዎች እና ማስረጃዎች” ማረጋገጡን ገልጿል።
በአካባቢዎቹ ላይ በአሁኑ ወቅት “የትጥቅ ግጭቶች” “እየተካሄዱ” መሆኑንም መንግስታዊው የሰብአዊ መብቶች ተቋም አመልክቷል። “እነዚህ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በትጥቅ ግጭት የተጎዱ እና በበቂ ሁኔታ ያላገገሙ በመሆናቸው፤ የትጥቅ ግጭት ዳግም መከሰቱ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ላይ ተደራራቢ ጉዳትን ሊያሳድር የሚችል በመሆኑ እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲልም ኢሰመኮ በመግለጫው አስገንዝቧል።

የትጥቅ ግጭቶቹ የዜጎችን “በህይወት የመኖር”፣ “የአካል ደህንነት”፣ “ከቦታ ቦታ የመዘዋወር” መብቶችን እንዲሁም የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑንም ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቁሟል። ኢሰመኮ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሰው፤ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ በረራዎች በመቋረጣቸው “በሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን” ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትግራይ ክልል ወደሚገኙት መቐለ፣ አክሱም እና ሽረ ከተሞች የሚያደርጋቸውን በረራዎች ማቋረጡን ያስታወቀው ከትላንት በስቲያ ረቡዕ መስከረም 13፤ 2019 ነበር። አየር መንገዱ በረራዎቹን “ለጊዜው” ያቋረጠው “በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ” ምክንያት መሆኑን በዚያኑ ዕለት ባወጣው መግለጫው አመልክቷል።
የአውሮፕላን በረራዎቹ የተቋረጡት፤ “ህወሓት ያሰማራቸው ታጣቂዎች” በሶስቱ ከተሞች የሚገኙ የአየር ማረፊያዎችን ካለፈው ማክሰኞ መስከረም 12 ጀምሮ በመያዛቸው መሆኑን ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው ጠቁሟል። ከትግራይ ክልል ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በየብስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች “ሙሉ ለሙሉ መቋረጣቸውን” በመግለጫው ያነሳው ኮሚሽኑ፤ በዚህም ሳቢያ በመሰረታዊ ቁሳቁሶች እና አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ “ክፍተቶች በመፈጠራቸው”፣ በክልሉ “የዋጋ ንረት” መከሰት መጀመሩን አብራርቷል።
በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች “የተቀሰቀሰው ግጭት” “እጅግ አሳሳቢ” መሆኑን የገለጹት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሀኑ አዴሎ፤ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች በተለይም የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት “ፈራሚ አካላት” “ስምምነታቸውን እንዲያከብሩ” አሳስበዋል። በግጭቱ የሚሳተፉ ኃይሎች፤ በሚያደርጓቸው “ማናቸውም እንቅስቃሴዎች እና ውሳኔዎች” በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ህጎች የተጣለባቸውን ግዴታዎች እንዲያከብሩም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽነር ብርሃኑ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች “የሲቪል ሰዎችን እና መሰረተ ልማቶችን ለጉዳት ከሚዳርጉ እርምጃዎች እንዲታቀቡ” ማሳሰባቸውንም ኢሰመኮ በመግለጫው ጠቅሷል። ሲቪል ሰዎች እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች “ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ” በመግለጫው አጽንኦት የሰጠው ኢሰመኮ፤ “የትጥቅ ግጭቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ” እና “ልዩነቶች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ” ጥሪ አቅርቧል።
የግጭቱ ተሳታፊ አካላት “ወደ ውይይት እንዲመለሱ”፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ” የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነርም ጥሪ ማቅረባቸው በመግለጫው ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]


































