የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ በስምንት ዓመት ገደማ፤ ለአራተኛ ጊዜ ሊሻሻል ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ወዲህ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ለአራተኛ ጊዜ ሊሻሻል ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ፤ ላለፉት ሶስት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በስራ ላይ የነበረውን ህግ የሚያሻሽል የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ እንዲተላለፍ ወስኗል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ሰኞ መስከረም 18፤ 2019 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ውሳኔ ካሳለፈባቸው አምስት ጉዳዮች ውስጥ፤ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅን የሚመለከተው አንዱ ነበር። ነባሩን አዋጁን በድጋሚ ማሻሻል ያስፈለገው፤ የመከላከያ ሰራዊት በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 87 ድንጋጌዎች መሰረት የተሰጡትን “ሃገራዊ ተልዕኮዎች በህግ አግባብ ለመፈጸም እንዲችል” መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ረፋዱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጽህፈት ቤቱ በመግለጫ በጠቀሰው የህገ መንግስት አንቀጽ ስር የተካተቱ አምስት ድንጋጌዎች፤ “የመከላከያ መርሆዎችን” የሚመለከቱ ናቸው። የመጀመሪያው ድንጋጌ “የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦች እና የህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል” ይላል። 

ሁለተኛው ድንጋጌ የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ግለሰብ “ሲቪል” መሆን እንዳለበት የሚያዝ ነው። “የመከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ መስረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል” የሚለው ደግሞ በሶስተኛ ንዑስ አንቀጽነት ተቀምጧል። 

በአራተኛ ድንጋጌነት በህገ መንግስቱ የሰፈረው፤ “የመከላከያ ሰራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለህገ መንግስቱ ተገዢ ይሆናል” የሚለው ነው። የመከላከያ ሰራዊት “ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነጻ በሆነ አካሄድ እንደሚያከናውን” የሚደነግገው ንዑስ አንቀጽም፤ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 87 አካል ነው።

በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት እንደተሻሻለ በተገለጸው የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ላይ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት “በሰፊው መወያየቱን” የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በመግለጫው አመልክቷል። ምክር ቤቱ በአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁ ላይ “ግብአቶችን በማከል” ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ “በሙሉ ድምጽ” እንደወሰነም የጽህፈት ቤቱ መግለጫ ጠቁሟል።

አዋጁ ለመጨረሻ ጊዜ በተወካዮች ምክር ቤት በተሻሻለበት ወቅት፤ ስድስት የፓርላማ አባላት ድምጽ ከመስጠት ታቅበው ነበር። ምክር ቤቱ የአዋጁን ማሻሻያ ያጸደቀው፤ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ የግጭት የማቆም ስምምነት በተፈራረሙ በጥቂት ወራት ልዩነት ነው።

በሚያዝያ 2015 ዓ.ም የጸደቀው የማሻሻያ አዋጁ፤ “የዘር ማጥፋት”፣ “የጦርነት ማቆም ወይም የሰላም ስምምነት ውልን ማፍረስ” እንዲሁም “በሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚፈጸሙ የጦርነት ወንጀሎችን የመዳኘት ስልጣን”፤በመከላከያ ሰራዊት ስር ለሚገኙ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ሰጥቷል። ማሻሻያው ከመጽደቁ ከወራት በፊት በፓርላማ በተደረገ ውይይት፤ “የወታደራዊ ፍርድ ቤቶችን” በተመለከተ በአዋጁ የተካተቱት አንቀጾች “እንደገና ሊታዩ እንደሚገባ” ሃሳብ ተሰጥቶ  ነበር።

አሁን በስራ ላይ የሚገኘው እና ማሻሻያ የተዘጋጀለት ነባሩ አዋጅ፤ ለመከላከያ ሰራዊት ከሰጣቸው ተልዕኮዎች አንዱ “የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ህገ-መንግሥቱን እና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ከውጭ ወራሪ እና ከውስጥ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ስጋት እና ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል” የሚል ነው። መከላከያ ሰራዊት “በምድር፣ በአየር፣ በባህር፣ በሳይበር እና በጠፈር መዋጋት በሚችል መልኩ” እንደሚደራጅም፤ በስራ ላይ ባለው የአዋጅ ማሻሻያ ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)