የኦሮሚያ ክልልን ስድስት ዞኖች ብቻ እንዲኖሩት አድርጎ ለማወቀር የሚያስችል አዋጅ ጸደቀ

የኦሮሚያ ክልል ስድስት ዞኖች ብቻ እንዲኖሩት የሚያደርግ አዲስ አደረጃጀት የተካተተበት አዋጅ በጨፌ ኦሮሚያ ጸደቀ። በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ላይ ዛሬ ሰኞ መስከረም 18፤ 2019 የጸደቀው አዋጅ፤ ለዞኖች “ለመጀመሪያ ጊዜ የህግ ማዕቀፍ እና የመወሰን ስልጣን የሰጠ ነው” ተብሏል።

ዛሬ ከሰዓት በተካሄደው የጉባኤው ውሎ በሙሉ ድምጽ የጸደቀው ይህ አዋጅ፤ “የኦሮሚያ ክልል ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች፤ የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን” የወጣ እንደሆነ ተገልጿል። እስከ ዛሬ በስራ ላይ የቆየው የክልሉ አደረጃጀት፤ የኦሮሚያ ክልልን በ21 ዞኖች ያዋቀረ ነበር።

አዲሱ አደረጃጀት ግን የኦሮሚያ ክልልን በአቅጣጫ ላይ በተመሰረቱ ዞኖች መልሶ የሚያዋቅር ይሆናል። በዚህ መሰረት አዳዲሶቹ ስድስት ዞኖች፤ “ምስራቅ”፣ “ምዕራብ”፣ “ማዕከላዊ”፣ “ደቡብ”፣ “ደቡብ ምዕራብ” እና “ደቡብ ምስራቅ” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

ይህን አደረጃጀት ስለያዘው አዋጅ ለጨፌ ኦሮሚያ አባላት ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጉዮ ዋሪዮ፤ የህግ ረቂቁ “በክልሉ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ሪፎርሞችን ለማስቀጠል” የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል። በኦሮሚያ የሚሰጡ አገልግሎቶች ወደ ታችኛው መዋቅር “እየወረዱ” መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጉዮ፤ የዞኖቹ አወቃቀር “ለአደረጃጀት፣ ቁጥጥር እና ክትትል የሚያመች” መሆኑን ተናግረዋል። 

አዲሱ አዋጅ በስድስቱ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ መስሪያ ቤቶችን ምንነት “በግልጽ ያስቀመጠ” መሆኑም ተገልጿል። “ለዞኖች ከፍተኛ የመወሰን ስልጣንን ይሰጣል” የተባለለት ይህ አዋጅ፤ የክልሉ መንግስት የሚገነባውን ስርዓት “በህግ የተጠናከረ እንዲሆን ያደርጋል” የሚል እምነት ተጥሎበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)