ከአንድ ሳምንት በፊት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፤ በፌደራል መስሪያ ቤት የሚኒስትር ዴኤታነት አዲስ ሹመት ተሰጣቸው። ከሁለት ሳምንት በፊት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዲሆኑ የተሾሙት ዶ/ር ቶላ በሪሶ፤ ባለፈው ቅዳሜ በተመሳሳይ መልኩ የሚኒስትር ዴኤታ ሹመት አግኝተዋል።
ለሁለቱም አመራሮች የሚኒስትር ዴኤታነት ሹመት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። አቶ ብርሃኑ በፌደራል የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሹመት ያገኙት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 3፤ 2019 ነው።
እርሳቸው ጨምሮ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሹመት የተሰጣቸው አመራሮች ሰባት ናቸው። ከሰባቱ ተሿሚዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ይገዙ፤ እንደ አቶ ብርሃኑ ሁሉ ከተመሰረተ ሶስት ዓመት ባስቆጠረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራር ነበሩ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ተስፋዬ፤ ከኃላፊነታቸው ተነስተው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው የተሾሙት በነሐሴ 2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበር። ባለፈው ቅዳሜ በተሰጠው የሚኒስትር ዲኤታዎች ሹመት ውስጥ ያልተካተቱት አቶ ተስፋዬ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ረዳት አስተባባሪ ሆነው በዛሬው ዕለት ተሹመዋል።
የሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ያለው ይህ ሹመት፤ ለዶ/ር መሃመድ እንድሪስም ተሰጥቷል። በተመሳሳይ መልኩ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ንቁ ተሳታፊ ወ/ት ፈዲላ ቢያ፤ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ የዲጂታል ሚዲያ አስተባባሪነት ሹመት አግኝተዋል። ፈዲላ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ እና የገዢው ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንትም ናቸው።
በዛሬው ዕለት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ከተሾሙት ሁለት አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ ብርሃኑ፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት የደቡብ ኢትዮጵያ የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። አቶ ብርሃኑ የጋሞ ዞን ዋና እና ምክትል አስተዳዳሪ ሆነውም አገልግለዋል።

አዲሱ ተሿሚ በፌደራል መስሪያ ቤት የሚኒስትር ዴኤታ ሹመት ከማግኘታቸው 11 ቀናት በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቢሮ ኃላፊነት ሹመት ተሰጥቷቸው ነበር። ለአቶ ብርሃኑ ይህንን ሹመት የሰጡት፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን እንዲመሩ ባለፈው መስከረም 22፤ 2019 በክልሉ ምክር ቤት የተሰየሙት ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።
እንደ አቶ ብርሃኑ ሁሉ በክልል ደረጃ ሹመት ካገኙ ከሳምንታት በኋላ የፌደራል ሚኒስትር ዴኤታነት ስልጣን ያገኙት ዶ/ር ቶላ በሪሶ ናቸው። የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮን ለዓመታት የመሩት ዶ/ር ቶላ በሪሶ፤ የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።
በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የሰጡት ይህ ሹመት፤ መስከረም 18፤ 2019 በተካሄደው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) ስብሰባ ላይ መጽደቁ ይታወሳል። በዚህ ስብሰባ ላይ ቃለ መሃላ የፈጸሙት ዶ/ር ቶላ በበነጋታው በትምህርት ቢሮ የነበራቸውን ኃላፊነት ለተተኪያቸው ዶ/ር ቡልቶሳ ሂርኮ አስረክበዋል።

እንደ ዶ/ር ቶላ ሁሉ አቶ ብርሃኑም አዲስ ከተሾሙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጋር ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የስራ ርክክብ አድርገዋል። የክልሉ የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ወንድሙ ሴታ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































