የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ ከተማ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ ከነገ በስቲያ ዳግም ሊጀምር ነው  

ላለፉት ሶስት ሳምንታት ተቋርጦ የቆየው በአዲስ አበባ እና በመቐለ ከተሞች መካከል የሚደረገው የአውሮፕላን መደበኛ በረራ፤ ከነገ በስቲያ እሁድ ጥቅምት 1፤ 2019 ጀምሮ በድጋሚ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ። አየር መንገዱ ደንበኞቹ የጉዞ ምዝገባቸውን ከዛሬ ጀምሮ ማካሄድ እንደሚችሉ ገልጿል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ ከተማ የሚያደርጋቸውን በረራዎች “በጊዜያዊነት” ያቋረጠው ከመስከረም 13፤ 2019 ጀምሮ ነበር። ለበረራዎቹ መቋረጥ በወቅቱ አየር መንገዱ የሰጠው ምክንያት በትግራይ ክልል ያለውን “ወቅታዊ ሁኔታ” ነው። 

አየር መንገዱ ከሶስት ሳምንት በፊት ያወጣው አጭር መግለጫ በክልሉ ያለውን ሁኔታ በግልጽ ያብራራ አልነበረም። ሆኖም በረራው በተቋረጠበት ዕለት በመቐለ ከተማ የሚገኘው አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያን ጨምሮ በሽረ እና አክሱም የሚገኙት አየር ማረፊያዎች በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሚታዘዙ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ለበረራ ማቋረጡ እንደ ዋነኛ ምክንያት ተወስዷል። 

የመቐለ ከተማ ጸጥታን ካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ ሲያስከብሩ የቆዩትም እነዚሁ ኃይሎች ነበሩ። የጸጥታ ኃይሎቹ ባለፈው ሳምንት አርብ መቐለን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና ራሳቸውን “የትግራይ ሰላም ኃይሎች” ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች በነጋታው ወደ ከተማይቱ ገብተዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት የመቐለ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያን መልሰው መቆጣጠራቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች፤ ባለፉት ቀናት በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲሰራጩ ታይተዋል። እንደ መቐለ ሁሉ ላለፉት ሶስት ሳምንታት በረራ ተቋርጦበት የቆየውን ሽረን ተቆጣጥረው የቆዩት በህወሓት የሚታዘዙ ኃይሎች፤ ከተማውን ትላንት ሐሙስ ለቅቀው መውጣታቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)