በትላንትናው ዕለት በተመሰረተው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩት የቀድሞዋ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ፤ በአፋር ክልል መንግስት ሹመት ተሰጣቸው። የመጀመሪያዋ ሴት የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አይሻ፤ የአፋር ክልል የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንን በኃላፊነት እንዲመሩ በዛሬው ዕለት መሾማቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
አራት የፌደራል መስሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት የመሩት አይሻ፤ ወደ ተወለዱበት አፋር ክልል የመለሳቸውን ኃላፊነት የሰጧቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ናቸው። አይሻ በሚኒስትርነት ከመሾማቸው አስቀድሞ የአፋር ክልል የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ቢሮ ኃላፊ ነበሩ።
የምህንድስና ባለሙያዋ አይሻ የመጀመሪያውን የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትርነትን ያገኙት በ2008 ዓ.ም. ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን በያዙ በጥቂት ወራት ልዩነት ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ ሹመት ከተሰጣቸው 10 ሴቶች አንዷ የነበሩት አይሻ፤ የመከላከያ ሚኒስትርነቱን ከአቶ ሞቱማ መቃሳ ተረክበዋል።
ሆኖም ሚኒስትሯ በዚህ የኃላፊነት ቦታቸው የሰሩት አንድ ዓመት ለማይሞላ ጊዜ ነበር። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፤ እርሳቸው ወደ ከተማ ልማት እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተዘዋውረዋል።
የከተማ ልማት እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ የመሩት አይሻ፤ በመስከረም 2014 ዓ.ም. በተካሄደው አዲስ የካቢኔ ምስረታ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። አይሻ በዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም በኃላፊነት የቆዩት ለሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወራት ብቻ ነው።
በግንቦት 2016 ዓ.ም. ከዚህ ኃላፊነታቸው ተነስተው፤ ቀድመው ለወራት የሰሩበትን መከላከያ ሚኒስቴርን በድጋሚ በሚኒስትርነት እንዲመሩ ተደርገዋል። አይሻ የለቀቁትን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የተረከቡት፤ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር አብርሃም በላይ ናቸው።
በመከላከያ ሚኒስትርነታቸው ለሁለት ዓመት ከአራት ወራት የዘለቁት አይሻ፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን ተከትሎ በትላንትናው ዕለት በተመሰረተው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ካቢኔ ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተዋል። ትላንት መስከረም ሐሙስ መስከረም 28፤ 2019 በተካሄደ የካቢኔ ሹመት፤ 12 ሹማምንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት አባልነታቸው እንዲቀጥሉ ተደርገዋል።
በትላንትናው ዕለት አይሻን በመተካት መከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት፤ ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የሰላም ሚኒስትር ሆነው በሰሩት በአቶ መሐመድ እድሪስ ነው። የቀድሞዋ እና አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት የስራ ርክክብ አድርገዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































