በትግራይ ክልል አብዛኞቹ ሆስፒታሎች ወደ ስራ መመለሳቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ገለጸ

በትግራይ ክልል ባለው ውጊያ እና ባጋጠማቸው የህክምና አቅርቦቶች እጥረት ምክንያት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች አቋርጠው የነበሩ “አብዛኞቹ ሆስፒታሎች” ወደ ስራ መመለሳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ። በክልሉ የጤና አገልግሎቶችን ወደነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ተጨማሪ መድኃኒቶች እና የህክምና አቅርቦቶች በመጓጓዝ ላይ እንደሆኑም ድርጅቱ ገልጿል።

ተመድ ይህን የገለጸው፤ የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ምክትል ቃል አቀባይ ፋራህን ሃቅ ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 5፤ 2019 በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ምክትል ቃል አቃባዩ በዚሁ መግለጫቸው፤ በሰሜን ትግራይ እና አፋር አካቢዎች እንዲሁም በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች ያለው ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም “አለመረጋጋት የሚታይበት” እንደሆነ ተናግረዋል። 

በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ በሲቪሎች እና በሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ “አደጋ መደቀኑን” የገለጹት ፋራህን፤ ሰብአዊ እርዳታን የማድረስ ሂደቱን “እንዲወሳሰብ” ማድረጉን አስረድተዋል። እንዲያም ሆኖ ተመድ እና የሰብአዊ አጋሮቹ፤ ወደ ትግራይ ክልል ተጨማሪ እርዳታ በማስገባት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት እና አጋሮቹ በአብዛኞቹ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎችም እርዳታዎች ማድረሳቸውን እንደሚቀጥሉም ፋራህን አመልክተዋል። ምክትል ቃል አቀባዩ ይህን ከመግለጻቸው አስቀድሞ፤ የተመድ የዓለም ጤና ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ በግጭት ለተጎዱ ማህበረሰቦች 71 ሜትሪክ ቶን መድኃኒቶች፣ የህክምና አቅርቦቶች እና ግብዓቶች መላካቸውን ገልጾ ነበር።

ለጤና አገልግሎት አንገብጋቢ የሆኑት ግብዓቶች የተላኩት በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ 49 መዳረሻዎች እንደሆነ በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ገልጿል። ድርጅቱ በከባድ መኪናዎች የተጫኑ ግብዓቶች ወደ ሶስቱ ክልሎች የላከው፤ ከተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) እና ከአውሮፓ ህብረት የሲቪል ጥበቃ እና ሰብአዊ እርዳታ ቢሮ በተገኘ ድጋፍ እንደሆነ አስታውቋል።

የተመድ ዋና ጸሀፊ ቃል አቃባይ ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎቶች “የመቋረጥ አደጋ ላይ መሆናቸውን” የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እንዳሳሰቧቸው ገልጸው ነበር። ቃል አቃባዩ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ዋቢ በማድረግ፤ የእነዚህ አገልግሎቶች መስተጓጎል በክልሉ ነዋሪ ላይ “የከፋ አደጋ የሚያስከትል” መሆኑንም አስጠንቅቀው ነበር።

የእርሳቸው ምክትል በትላንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ ባለው ውጊያ እና ባጋጠማቸው የህክምና አቅርቦቶች እጥረት ምክንያት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች አቋርጠው የነበሩ “አብዛኞቹ ሆስፒታሎች” ወደ ስራ መመለሳቸውን ገልጸዋል። ወደ ስራ ከተመለሱት ውስጥ በትግራይ ክልል ዋና ከተማ በመቐለ የሚገኘው አይደር ሆስፒታል እንደሚገኝበትም አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)