የሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አጀንዳዎች እና ምክረ ሃሳቦች በአንድ ሳምንት ገደማ ጊዜ ውስጥ ለፓርላማ ሊቀርቡ ነው 

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ የቀረቡ አጀንዳዎችን እና መፍትሔ አመንጪ ምክረ ሐሳቦችን ከመስከረም 10፤ 2019 በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ አጀንዳዎቹን እና ምክረ ሃሳቦቹን ለሁሉም ክልሎች እና ለፌደራል መንግስት የማስረከብ ስራ እንደሚሰራም ገልጿል። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው፤ በቀጣይ የሚሰራቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ ጳጉሜ 5፤ 2018 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በአዲስ አበባ በሚገኘው የተቋሙ ዋና ጽህፈት ቤት መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ከሰሞኑ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የቀረቡ አጀንዳዎችን እና ምክረ ሃሳቦችን የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን መንግስት ምክረ ሃሳቦቹን በተግባር ላይ ለማዋል የሚረዳውን የዕቅድ ስትራቴጂ ማዘጋጀት ስራዎች እየተከናወነ እንደሆነም ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በ2014 ዓ.ም የወጣው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ኮሚሽኑ “የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ስልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት” ለአስፈጻሚ አካሉ እንደሚያቀርብ ደንግጓል።

ኮሚሽኑ ይህንኑ ሰነድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብም በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በዛሬው መግለጫቸው፤ አጀንዳዎቹን እና ምክረ ሃሳቦቹን የያዘው ሰነድ በመጪዎቹ ዘጠኝ ቀናት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት ሰነዱን የሚረከበው፤ በሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተመረጡት የፓርላማ አባላት የስራ ዘመናቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ነው። በኢፌዲሪ ህገ መንግስት መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ተካሄዶ የሚጠናቀቀው፤ ነባሩ ፓርላማ የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት ነው።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አጀንዳዎች እና ምክረ ሃሳቦች ከአስፈጻሚ አካሉ እና ከፓርላማ በተጨማሪ “ሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት” እንደሚቀርብ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሰፍሯል። በዚህ መሰረት ኮሚሽኑ አጀንዳዎቹን ለሁሉም ክልሎች የማስረከብ ስራ እንደሚሰራ ፕሮፌሰር መስፍን በዛሬው መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።

“ከህዝቦቻችን የሰበሰብናቸውን፣ ከየወረዳው ያመጣናቸውን፣ ክልሎችን እና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮችን በተለየ የሚመለከቱ፤ ሁለተኛ ደግሞ ትግራይ [ክልልን] የተመለከተ በርካታ የሆኑ አጀንዳዎች ሰብስበናል። ትግራይን በተመለከተ ልክ እንደሌሎቹ 11 ክልሎች ሁሉ፣ ለ12ኛውም የትግራይ ክልል [አጀንዳዎችን] ማስረከብ ይኖርብን ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ያለውን፣ ትግራይን በተመለከተ ያለውን ታውቃላችሁ። ስለዚህ እነሱን አጀንዳዎች ለፌደራል መንግስት እናስረክባለን” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ በቀጣይ የሚከናወነውን አስረድተዋል።

ክልሎች የሚረከቧቸው አጀንዳዎች፤ በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ለሚደረጉ ምክክሮች (intradialogue regional dialogue) አሊያም የክልሉ መንግስት ሊፈጽማቸው የሚገቡ “ትክክለኛ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች” እንደሆኑም ፕሮፌሰር መስፍን አብራርተዋል። እነዚህን አጀንዳዎች ኮሚሽኑ ለማስረከብ ያቀደው በመጪው መስከረም 10 እንደሆነም ጥቆማ ሰጥተዋል። 

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው አጀንዳዎች እና ምክረ ሃሳቦች መቼ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ አጀንዳዎቹ እና ምክረ ሃሳቦቹ በኮሚሽኑ አማካኝነት ለህዝብ ይፋ መደረግ እንዳለባቸው ደንግጓል።

ከሐምሌ 1 እስከ ነሐሴ 16፤ 2018 ድረስ በአዲስ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ከ400 አጀንዳዎች በላይ ለውይይት መቅረባቸውን ኮሚሽኑ መግለጹ ይታወሳል። ከእነዚህ አጀንዳዎች ውስጥ የጋራ ስምምነት ሳይደረስባቸው የተጠናቀቁት አራቱ ብቻ መሆናቸውንም ኮሚሽኑ በወቅቱ አስታውቋል። 

በምክክር ጉባኤው ስምምነት ሳይደረስባቸው በልዩነት ከተያዙት ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ እና የመንግስት አደረጃጀትን የሚመለከቱት ይገኙበታል። በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከአራት ሺህ በላይ ተመካካሪዎች ተሳትፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]