ባለፈው የፈረንጆቹ 2025 ዓመት በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ 1,680 ጥቃቶች ውስጥ መፈጸማቸውን የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) ገለጸ። ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ አስራ ዘጠኙ የተፈጸሙት በኢትዮጵያ መሆኑን፤ ተቋሙ ያጣቀሰው በቅርቡ በመንግስታቱ ድርጅት በኩል የቀረበ አንድ ሪፖርት አመልክቷል።
ዩኔስኮ ባለፈው ሰኔ ወር በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የቀረበውን ሪፖርት ያጣቀሰው፤ ዛሬ ረቡዕ ጳጉሜ 3፤ 2018 የታሰበውን “ትምህርትን ከጥቃት የመከላከል ዓለም አቀፍ ቀን” በማስመልከት ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፤ ከቀደመው ዓመት በ33 በመቶ መጨመራቸውን ዩኔስኮ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።
የድርጅቱ ዳይሬክተር ጄኔራል ኻሊድ ኢል-ኢንናኒ “የህጻናትን ደህንነት፣ ትምህርትና ተስፋ የሚነጥቁ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መመጨመራቸው በጥልቅ” እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል። ዩኔስኮ ለዚህ በማሳያነት በመግለጫው የጠቀሰው፤ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ህጻናት ላይ 38,558 ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ማረጋገጡን ነው።

ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል 130 ያህሉ የደረሱት በኢትዮጵያ ባሉ ህጻናት ላይ መሆኑን ተመድ ማረጋገጡን የሰኔው ሪፖርት ያሳያል። የአካል ጉዳት እና ጾታዊ ጥቃትን ያካተቱት እነዚህ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙት በ72 ኢትዮጵያውያን ህጻናት ላይ መሆኑንም ሪፖርቱ አትቷል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ የተመድ ሪፖርት፤ ከታህሳስ 2017 እስከ ታህሳስ 2018 ዓ.ም. ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 45 ኢትዮጵያውያን ህጻናት መገደላቸውን እና ሌሎች 23 ህጻናት ላይ አካላዊ ጉዳት መድረሱን አመልክቷል። ህጻናት ከተገደሉባቸው እና የአካል ጉዳተኛ ከሆኑባቸው ጥሰቶች ውስጥ ሃያ አራቱ በመከላከያ ሰራዊት የተፈጸሙ እንደሆኑ በዚሁ የተመድ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል።
ለአራት ጥቃቶች የትግራይ ፖሊስን ተጠያቂ ያደረገው ሪፖርት፤ አንድ ሌላ ጥቃት በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እንደተፈጸመ ጠቁሟል። በኢትዮጵያ ህጻናት ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች መካከል አስራ ስድስቱ የተፈጸሙት “ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች” እንደሆነም በሪፖርቱ ላይ ተቀምጧል።
ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ከተገደሉት ህጻናት መካከል 10 ህጻናት በፈንጂዎች እና በተተኳሾች ህይወታቸውን ማጣታቸው በሪፖርቱ ተሰንዷል። በዚሁ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ አምስት ህጻናት በተባራሪ ጥይት መገደላቸውን ተመድ በሪፖርቱ መዝግቧል።
ይኸው ሪፖርት በህጻናት ላይ ከተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪ በሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ዘርዝሯል። ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በኢትዮጵያ ባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ የተፈጸመው ጥቃት 19 እንደሆነ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በሆስፒታሎች ላይ 14 ጥቃቶች መድረሳቸውን ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያን በተመለከተው የሪፖርቱ ክፍል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በተወሰኑ ክልሎች ያለው ውጥረት” በህጻናት ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ እንደሚያሰጋቸው ገልጸዋል። ዋና ጸሀፊው “አሳሳቢ” ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ ግድያዎች፣ አካል ማጉደል፣ አፈና፣ በትምህርት ቤቶች እና በሆስፒታሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲሁም ተቋማቱን ለወታደራዊ አገልግሎት መጠቀም የሚሉት ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































