ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ ከ600 በላይ እስረኞች መፈታታቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የቀድሞው የኢዜማ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደን ጨምሮ ከ600 በላይ እስረኞች፤ ክሳቸው እንዲቋረጥ በማድረግ እና በይቅርታ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሐሙስ ጳጉሜ 5፤ 2018 በዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

መግለጫውን የሰጡት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ፤ የክስ ሂደታቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኙ እና ፍርድ የተሰጠባቸው እስረኞች “ባቀረቡት ጥያቄ” መሰረት እንደሆነ ተናግረዋል። በማረሚያ ቤት በእስር ላይ ከሚገኙ ግለሰቦች መካከል የተወሰኑት፤ መንግስት “ያሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ በልዩ ሁኔታ ከእስር እንዲፈታቸው” በኢሰመኮ በኩል ጥያቄ ማቅረባቸውንም አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ያቀረበውን ጥያቄ የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ “ለሰላም፣ ለሀገራዊ መግባባት፣ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም ጥያቄ ተቀብለው ሊያስተናግዱ ፍቃደኛ መሆናቸውን” ለተቋሙ መግለጻቸውን አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ አቋማቸውን የሚያንጸባርቅ “ትዕዛዝ” በሚመሩት መንግስት ስር ላሉ መዋቅሮች ማስተላለፋቸውንም አክለዋል።

ይህንን ተከትሎ ኢሰመኮ ላለፉት አምስት ወራት የእስረኞቹን ጉዳይ “ሲከታተል” መቆየቱን ዋና ኮሚሽነሩ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። “ጥያቄን ያቀረቡ በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ጥያቄዎች ተቀብለን ለመንግስት በማቅረብ፤ ከመንግስት ደግሞ የሚነሱ ቅድመ ሁኔታዎችን ለእስረኞቹ በማቅረብ፤ በእንግሊዘኛው አባባል shuttle negotiation ስናደርግ ነው የቆየነው” ሲሉ አቶ ብርሃኑ ሂደቱን አብራርተዋል።

መንግስታዊው የሰብአዊ መብት ተቋም ሲያካሄድ የቆየው “የማግባባት” ሂደት ውጤታማ ሆኖ፤ በዛሬው ዕለት ከ600 በላይ እስረኞች ከእስር እንዲወጡ መደረጋቸውን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ተናግረዋል። ከእነዚህ እስረኞች መካከል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና ዶ/ር ካሳ ተሻገር እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል።

ላለፉት ሶስት ዓመታት ያህል በእስር ላይ የቆዩት አቶ ክርስቲያን ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት የተፈቱት ዛሬ ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ገደማ እንደነበር ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እነ አቶ ክርስቲያን ከእስር ከመለቀቃቸው ከሁለት ቀናት በፊት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተገኝተው እንዳነጋገሯቸው እኚሁ ምንጮች ገልጸዋል።

ከቋሪት ምርጫ ክልል አብንን ወክለው የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ባሳለፈበት ዕለት ሐምሌ 28፤ 2015 ነበር። በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን በመወከል የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት በተመሳሳይ ቀን እንደነበር ይታወሳል።

ከሁለቱ ፖለቲከኞች ጋር በተመሳሳይ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ዶ/ር ጫኔ በፖሊስ የተያዙት መስከረም 13፤ 2016 እንደነበር በወቅቱ በሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩት ኢዜማ ፓርቲ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ዶ/ር ጫኔ፣ ዶ/ር ካሳ እና አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ 52 ተጠርጣሪዎች የተካተቱበት የሽብር ወንጀል ክስ ላለፈው ሶስት ዓመት በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል። 

የፍርድ ሂደቱ መዘግየትን በተመለከተ ተከሳሾቹ በተደጋጋሚ ቅሬታዎች እና አቤቱታዎችን ለችሎት ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። ተመሳሳይ አቤታቱዎች በፓርላማ ስብሰባዎች ላይ ጭምር በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሲስተጋቡ መቆየታቸውም አይዘነጋም።

የፍትህ ሚኒስትሯ ሀና አርዓያሥላሴ በተገኙበት የፓርላማ ስብሰባ ላይ፤ በተከሳሾቹ ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲቋረጥ ጥያቄ ቀርቦም ነበር። የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ ምክር ቤት ተመራጮች የሆኑት ተከሳሾች ባለፈው ጥር ወር ችሎት በቀረቡበት ወቅት ያለመከሰስ መብታቸው ከሕግ ውጭ መነሳቱን ጠቅሰው፤ በዐቃቤ ህግ የቀረቡባቸው ማስረጃዎች ውድቅ ተደርገው “በነፃ እንዲሰናበቱ” መጠየቃቸውም ይታወሳል።

ከእነዚሁ ተከሳሾች የተወሰኑት በፍርድ ቤት እየታየ ያለው የክስ ሂደታቸው “በልዩ ሁኔታ” ታይቶ መንግስት ከእስር እንዲፈታቸው ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር በዛሬው መግለጫቸው ላይ አንስተዋል። ኢሰመኮ ሲያካሄደው በቆየው “የማግባባት” ሂደት ውስጥ በመንግስት የቀረበላቸውን የይቅርታ ቅድመ ሁኔታ ያልተቀበሉ የሽብር ተከሳሾች እንዳሉ ለጉዳይ ቅርበት ያላቸው አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል አራቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንደሆኑም ምንጩ አመልክተዋል። ጋዜጠኞቹ ዳዊት በጋሻው፣ ጎበዜ ሲሳይ ገነት አስማማው፣ ከ“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት መስከረም አበራን ጨምሮ በአጠቃላይ 28 ተከሳሾች የይቅርታ ቅድመ ሁኔታውን አለመቀበላቸውን ምንጩ አክለዋል።

የእነዚህን 28 እስረኞች ዝርዝር ያውቁ እንደሆነ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው ኮሚሽነር ብርሃኑ፤ እስረኞቹ ጥያቄውን ባለማቅረባቸው ምክንያት በስም እንደማያውቋቸው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]