በኢትዮጵያ “አካታች የሽግግር መንግስት” ለመመስረት ያለመ ትብብር መመስረቱ ይፋ ተደረገ

በኢትዮጵያ “አካታች የሽግግር መንግስት” ለመመስረት ያለመ የሰባት አማጽያን ኃይሎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ትብብር መመስረቱ ይፋ ተደረገ። “የኢትዮጵያ ህዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለህልውና” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ይህን ትብብር ከመሰረቱት ውስጥ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው ዛሬ እሁድ መስከረም 10፤ 2019 በትግራይ በሚገኙ ዜና ማሰራጫዎች በኩል በተላለፈ መግለጫ ነው። መግለጫውን በንባብ ያቀረቡት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው አማጺ ቡድን አፋብንን በሊቀመንበርነት የሚመሩት አቶ ዘመነ ካሴ ናቸው። 

አቶ ዘመነ “ትብብር ለህልውና” የሚል አጭር መጠሪያ የሚጠቀመው የጋራ ትብብር ሰብሳቢ መሆናቸውም በቪዲዮ በተሰራጨው መግለጫ ላይ ተመልክቷል። የእዚሁ ትብብር ሌሎች መስራች አባላት፤ የኦጋዴን ህዝብ ነጻነት ግንባር፣ የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር፣ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ እና የጉሙዝ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ እንደሆኑም በመግለጫው ተጠቁሟል።

ከብዙ “ጥረት” እና “ውጣ ውረድ” በኋላ መመስረቱ የተነገረለት የጋራ ትብብር “የመጀመሪያ ግብ”፤ “በሽግግር ቻርተር” የሚመራ “አካታች የሽግግር መንግስት” እንዲመሰረት ማድረግ መሆኑን በመግለጫው አጽንኦት ተሰጥቷል። አቶ ዘመነ “አዲስ የሽግግር ምዕራፍ” ሲሉ በመግለጫቸው የጠሩት ይህ ሂደት፤ “የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲረጋግጡ የሚያስችል” እንደሆነም አስታውቀዋል።

ይህ “አዲስ ምዕራፍ” የሚከፈተው፤ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን እና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን ስርአት “በማስወገድ” መሆኑንም አቶ ዘመነ በመግለጫቸው አስገዝበዋል። ትብብር መፍጠራቸውን የገለጹት አማጽያን ኃይሎቹ እና የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያዋልዱት “የሽግግር ምዕራፍ”፤ ሁለት ዋነኛ ዓላማዎች ያሉት እንደሆነ ተገልጿል። 

ከእነዚህ ዋነኛ ዓላማዎች ቅድሚያ የተሰጠው “የህዝቦችን ህልውና እና የሀገርን ደህንነት መታደግ” የሚለው ጉዳይ ነው። ይህን ተከትለው የተዘረዘሩት ጉዳዮች በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ ያሉ “ሁሉንም ጦርነቶችን ማስቆም”፣ “ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማረጋገጥ” እና “ሰላምና ጸጥታን ማስጠበቅ” የሚሉት ናቸው።

“ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ማረጋጋት”፣ “ከጎረቤት ሃገር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል” እና “የሃገሪቱን ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ቁመና ማስተካከል” የሚሉትም በመጀመሪያው ዋነኛ ዓላማ ስር ተካትተዋል። “ትብብር ለህልውና” በሁለተኛ ዋና ዓላማነት በመግለጫው የጠቀሰው ጉዳይ፤ “ህዝባዊ እና ህገ መንግስታዊ ውይይት” (constitutional dialogue) ማድረግን ነው።

ለኢትዮጵያ “ሰላም” እና “ለህዝቦች ቀጣይ ህልውና” ሲባል እንደሚደረግ የተገለጸው ይህ ውይይት፤ “ሃቀኛ፣ ታማኝ፣ ሁሉንም ያካተተ እና ያሳተፈ” እንደሚሆን በመግለጫው ላይ ተመልክቷል። የውይይቱ ዓላማም “ወሳኝ ህዝባዊ እና ሀገራዊ ጥያቄዎችን በህዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ መመለስ” እንደሆነም አቶ ዘመነ በመግለጫው አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በፓርላማ እንዲቋቋም ሲያደርግ ተመሳሳይ ሃሳብን በማንገብ ነበር። ለኮሚሽኑ ማቋቋም መንስኤው፤ “በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተጠቅሷል።

“መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች” ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች፣ “ወሳኝ ምክንያቶችን” በመለየት እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት “ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት” ሚና በአዋጅ የተሰጠው ኮሚሽኑ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባዘጋጀው ጉባኤ ከ400 አጀንዳዎች በላይ ለውይይት መቅረባቸውን አስታውቆ ነበር። በጉባኤው ላይ የቀረቡ አጀንዳዎች እና ምክረ ሃሳቦች፤ ለፓርላማ፣ ለፌደራል መንግስት እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሌሎች የመንግስት አካላት እንደሚቀርቡ ኮሚሽኑ ከሳምንት በፊት በሰጠው መግለጫ አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]