አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን እንዳይጓዙ አስጠነቀቀች

የአሜሪካ መንግስት ሰራተኞች “ያለ ልዩ ፈቃድ” በሶማሌ ክልል ወደሚገኘው ዶሎ ዞን መጓዝ እንደማይችሉ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ “ጥብቅ ማስጠንቀቂያ” ሰጠ። ኤምባሲው ክልከላውን ይፋ ያደረገው በዞኑ የውጭ አገር ዜጎች ባለባቸው “ከፍተኛ ስጋት” ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 06፤ 2019 ምሽት ባሰራጨው የጉዞ ማስጠንቀቂያ መልዕክት፤ በዶሎ ዞን አሜሪካውያንን ጨምሮ በውጭ አገር ሰዎች ላይ ጥቃቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ መረጃ እንዳለው ይፋ አድርጓል። በዚህ ምክንያት አሜሪካውያን ወደ ዞኑ መጓዝ እንደማይመከሩም ገልጿል።

ኤምባሲው በዛሬው ማስጠንቀቂያው፤ አሜሪካውያን “ከአካባቢው እንዲርቁ” እና “ንቁ ሆነው እንዲጠባበቁ” አሳስቧል። የሀገሪቱ ዜጎች ከዚህ በተጨማሪ የተሰበሰበ ህዝብ ካለባቸው አካባቢዎች መራቅ፣ አካባቢያቸውን በንቃት መከታተል፣ ከአካባቢው ለመውጣት አማራጭ ዕቅዶች ማዘጋጀት እንዲሁም ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ያዘጋጇቸውን ዕቅዶች መከለስ እንዳለባቸው ከኤምባሲው ምክር ተላልፎላቸዋል።

አሜሪካ ዋና ከተማውን በዋርዴር ያደረገውን የዶሎ ዞን በተመለከተ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ከመስጠቷ አስቀድሞም ዜጎቿ ወደ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢው የሚያደርጉትን ጉዞ መልሰው እንዲያጤኑ ስትመክር ቆይታለች። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን በተመለከተ ባለፈው ነሐሴ ወር ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ “አለመረጋጋት፣ ወንጀል፣ እገታ፣ ሽብርተኝነት፣ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ እና የመገናኛ ዘዴዎች መቋረጥ እና ከሀገሪቱ ለመውጣት መከልከል” ስጋቶች እንደሆኑ ዘርዝሯል። 

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ “ደረጃ 3” በሚለው ምድቡ ባስቀመጠው በዚሁ ማስጠንቀቂያ “በሽብርተኝነት እና የአለመረጋጋት” ስጋት ምክንያት ወደ ተወሰኑ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች የአሜሪካ ዜጎች እንዳይጓዙ ከልክሎ ነበር። የጉዞ ማስጠንቀቂያው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ በምትዋሰንባቸው አካባቢዎችም፤ በሽብርተኝነት፣ እገታ እና የተቀበሩ ፈንጂዎች ምክንያት መጓዝ እንደማይቻል ይከለክላል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)