የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ሂደትን የማገዝ ስራ ለመቀጠል “ቁርጠኛ” መሆኑን አስታወቀ 

የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት የተፈራረሙትን የፕሪቶሪያ የግጭት የማቆም ስምምነትን አተገባበር ማገዝ “በጣም ወሳኝ” እንደሆነ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴዎዬ ተናገሩ። የስምምነቱ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ቢገባም፤ ኮሚሽነሩ የአፍሪካ ህብረት የአፈጻጸሙን “ሂደት የማገዝ ስራውን ለመቀጠል ቁርጠኛ” እንደሆነ ገልጸዋል።

ናይጄሪያዊው ዲፕሎማት በፌደራል መንግስት እና ህወሓት በሚመራው የትግራይ ክልል መካከል ባለው ብርቱ ውጥረት ምክንያት ህልውናው አደጋ ውስጥ የወደቀውን ስምምነት ያነሱት፤ ዛሬ ማክሰኞ በጅቡቲ በተጀመረው የኢጋድ አስቸኳይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው። ስብሰባው በቀጠናው የሚታዩ “የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታዎች ለመገምገም እየተካሄዱ ያሉ ጥረቶችን ለመፈተሽ”  ለኢጋድ አባል አገራት ዕድል እንደሚፈጥር ክፍለ አህጉራዊው ድርጅት ቀደም ብሎ አሳውቆ ነበር።

ስብሰባው የሚካሄደው በአባል አገራት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከቀጠናው እጅግ ርቀው የሚካሄዱ ጦርነቶች፤ በወደቦች፣ የነዳጅ ማደያዎች፣ የእህል ገበያዎችና የሰብአዊ ርዳታ በጀት ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ በሚገኙበት “አስቸጋሪና ፈታኝ” ወቅት እንደሆነ የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ተናግረዋል። ከኢጋድ አባላት መካከል አንዷ የሆነችው ሱዳን፤ በዓለም አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ የተከሰተባት ሀገር እንደሆነች ዋና ጸሀፊው ጠቅሰዋል።

ዶ/ር ወርቅነህ የዛሬውን ስብሰባ በከፈቱበትን ንግግራቸው ላይ በኢትዮጵያ ስላንዣበበው የጦርነት ስጋት ያሉት ነገር የለም። የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ አህጉራዊውን ተቋም እንደሚያሳስበው እና ችግሩን በውይይት ለመፍታት “ጥረት” እያደረገ መሆኑን በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ህብረት ጥረት ከኢጋድ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች “ሰላም ወዳድ” ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር “በተቀናጀ መልኩ” የሚደረግ እንደሆነም አስረድተዋል። ባንኮሌ በመጪው ጥቅምት ወር ከተፈረመ አራተኛ ዓመቱን በሚደፍነው የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበር የአፍሪካ ህብረት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚገፋበትም አክለዋል።

የህብረቱ ጥረት በአሜሪካ እና በአውሮፓ ሀገራት ድጋፍ ቢሰጠውም፤ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ የማሸማገል ሙከራዎች በማድረግ ላይ የሚገኙት የናይጄሪያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ግን በህወሓት በኩል የገለልተኝነት ጥያቄ ተነስቶባቸዋል። የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ የሆኑት ኦባሳንጆ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል የግጭት ማቆም ስምምነት እንዲፈረም ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)