በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት፤ በፌደራል መንግስት “ተከፈተብኝ” ያለውን “ወረራ” ለመመከት የክልሉን “ሰራዊት” “መመሪያ ሰጥቶ” ማሰማራቱን አስታወቀ። በክልሉ የሚካሄዱ የወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ ዘመቻዎችን እና ኦፕሬሽኖችን የሚመለከቱ መረጃዎችን፤ ከሚመለከተው አካል ውጪ ማሰራጨት “ህጋዊ ተጠያቂነት የሚያስከትል” መሆኑንም የክልሉ መንግስት አስጠንቅቋል።
በፌደራል መንግስት ዕውቅና የተነፈገው በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት ይህንን ያስታወቀው፤ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 13፤ 2019 ባወጣው መግለጫ ነው። የክልሉ መንግስት መግለጫው ያወጣው፤ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከትላንትና ጀምሮ “ጥቃቶች” እና “ውጊያዎች” እየተካሄዱ መሆኑ በተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይፋ መደረጉን ተከትሎ ነው።
“ጥቃቶቹ” እና “ውጊያዎቹ” በአላማጣ ከተማ እና አካባቢው እንዲሁም በትግራይ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎችን ያካለሉ እንደነበሩ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የትግራይ ክልል መንግስት በዛሬው መግለጫው፤ በትላንትናው ዕለት “በአውሮፕላን፣ በድሮኖች እና መድፎች ከባድ ድብደባ ሲካሄድ ውሏል” ብሏል።

የክልሉ መንግስት በዛሬው ዕለት “ተከፈተብኝ” ያለው ጥቃት፤ “በእግረኛ ወታደሮች የታጀበ ነው” ሲል ወንጅሏል። ይህን ውንጀላ በተመለከተ እስካሁን ድረስ በፌደራል መንግስት በኩል በይፋ የተሰጠ ምላሽ ባይኖርም፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአፍሪካ ቀንድ አማካሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን የህወሓት አመራሮች በአፋር እና በአማራ በሚገኙ የመንግስት ይዞታዎች ላይ ዛሬ ጠዋት “የተቀናጀ ጥቃት” መክፈቱን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል መንግስት በዛሬው መግለጫው፤ የክልሉ “ሰራዊት” “ጥቃት እና ወረራውን ለመመከት” መመሪያ እንደተሰጠው ገልጿል። ይህን ተከትሎም የትግራይ ክልል “ሰራዊት” “ወደ ውጊያ መግባቱን” ያረጋገጠው የክልሉ መንግስት፤ ውጊያውን በተመለከተ በሚመለከታቸው አካላት “ወቅታዊ ማብራሪያ” በየጊዜው የሚሰጥ መሆኑንም አመልክቷል።
ከእነዚህ አካላት ውጪ “የወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ ዘመቻዎችን እና ኦፕሬሽኖችን የሚመለከቱ” መረጃዎች ማሰራጨት “ህጋዊ ተጠያቂነት የሚያስከትል” እንደሆነ የክልሉ መንግስት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በ2012 ዓ.ም. ተመርጦ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር መጨረሻ ወደ ስራ እንዲመለስ የተደረገው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ያጸደቀው አወዛጋቢ ህግ፤ እነዚህን መሰል ጥፋቶች “ፈጽመው ተገኝተዋል” በሚባሉ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ ቅጣት ይጥላል።
“የትግራይን ህዝብ ህልውና እና ደህንነት ለማረጋገጥ” ያለመ ነው የተባለለት ይህ ህግ፤ በጦርነት ጊዜ ከጠላት ጋር መተባበር እና ምስጢር ማሹለክ “ሆን ተብሎ ከተፈጸመ” “በዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት ሊያስቀጣ” እንደሚችል ደንግጓል። ህጉ በትግራይ “ሰራዊት ላይ ጉዳት ማድረስ” ሲል የሚያስቀምጠው ወንጀልም፤ ተመሳሳይ ቅጣት ያስከትላል።
በትግራይ ክልል እየተባበሰ የመጣው የጸጥታ ሁኔታ፤ ወደ መቐለ፣ አክሱም እና ሽረ ከተሞች የሚደረጉ በረራዎች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ፤ “በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት” ወደ ሶስቱ ከተሞች የሚደረጉ በረራዎች ከዛሬ ጀምሮ “ለጊዜው” የተቋረጡ መሆኑን አስታውቋል።
በመቐለ ከተማ የሚገኘውን የአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ የትግራይ ኃይሎች መቆጣጠራቸውን በከተማው የሚገኙ ምንጮች ዛሬ ጠዋት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። ከፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት በኋላ የአየር ማረፊያው ጸጥታ ሲጠበቅ የቆየው፤ በፌደራል ፖሊሶች ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል]

































