ለትግራይ የጸጥታ ሁኔታ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ትኩረት ነፍገዋል” ሲሉ አሜሪካዊው የኮንግረስ አባል ተቹ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በፍጥነት እየተባባሰ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ትኩረት ነፍገዋል” ሲሉ በዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የዴሞክራቶች ተወካይ ግሪጎሪ ሚክስ ነቀፉ። በኢትዮጵያ ባለው የሰብአዊ ሁኔታዎች እና የሰብአዊ መብቶች ቀውስ ምክንያት፤ አሜሪካ ጥላው የነበረው ማዕቀብ አለመራዘሙን የኮንግረስ አባሉ ተችተዋል።

በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ አሜሪካ በኤርትራ ላይ ጥላው የነበረው ማዕቀብ የመጨረሻ ቀነ ገደብ አርብ መስከረም 8፤ 2019 ነበር። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ማዕቀቡ እንዲጣል በመስከረም 2014 ዓ.ም. ትዕዛዝ ያስተላለፉት፤ የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ባዳረሰው ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶች ለአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ “ያልተለመደ እና ልዩ ስጋት ፈጥረዋል” በሚል ነበር።

የባይደን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የኢትዮጵያን “ሰላም፣ ጸጥታ ወይም መረጋጋት” የሚያሰጉ “እርምጃዎች ወይም ፖሊሲዎች” የሚያራምዱ ኃይሎች ላይ ዒላማ ያደረገ ነበር። በዚሁ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የኤርትራ መንግስት እና የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ (ሕግደፍ)፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የአማራ ክልላዊ መንግስት፣ የአማራ ክልላዊ እና መደበኛ ያልሆኑ ኃይሎች ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል መዘርዘሩም የሚታወስ ነው።

ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትን እና ህወሓትን ለማደራደር ከፍተኛ ግፊት በማድረግ ላይ በነበረችበት ወቅት በተጣለው ማዕቀብ በቀጥታ ስማቸው የተጠቀሰው፤ ሁለት የኤርትራ ባለስልጣናት እና አራት የአገሪቱ ተቋማት ናቸው። ማዕቀቡ እንዲጣል ያደረገው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ፤ በጆ ባይደን የስልጣን ዘመን ለሶስት ጊዜ ታድሷል።

ማዕቀቡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ በጳጉሜ 2017 ዓ.ም. ለአራተኛ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጎ ነበር። በየዓመቱ ሲታደስ የቆየው ማዕቀብ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለማራዘም፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የማዕቀቡ ቀነ ገደብ ከመድረሱ በፊት ባሉት 90 ቀናት ውስጥ ይህንኑ ውሳኔያቸውን ለአሜሪካ ኮንግረስ ማሳወቅ ነበረባቸው። 

ይሁንና አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን “አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም” እና ጥቅሟን ለማስጠበቅ በሚል ማዕቀቡን ላለማራዘም ወስናለች። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጋር “በጋራ የምትሰራበት ጊዜ ደርሷል” ሲሉ ከውሳኔው ጀርባ ያለውን ምክንያት ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (ኤ ኤፍ ፒ) አስረድተዋል።

ማዕቀቡ ሳይራዘም የቀረበት አካሄድ ግን በ72 ዓመቱ የኒውዮርክ የኮንግረስ አባል ግሪጎሪ ሚክስ ትችት ገጥሞታል። ሚክስ የማዕቀቡን ማብቃት በማስመልከት ትላንት ሰኞ መስከረም 11፤ 2019 ባስተላለፉት መልዕክት፤  ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “በከፍተኛ የግጭት ስጋት” ውስጥ እንደሚገኙ አስጠንቅቀዋል።

“ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሁለቱም ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ቀጠናዊ ሰላም እና መረጋጋትን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል” የሚሉት ዴሞክራቱ የኮንግረስ ተመራጭ፤ ማዕቀቡ እንዲያበቃ መደረጉን ኮንነዋል። “እነዚህን ማዕቀቦች አሁን ማንሳት የተሳሳተ መልዕክት በተሳሳተ ጊዜ ያስተላልፋል” ሲሉም አስገንዝበዋል። 

ሚክስ በሳምንቱ መጨረሻ ተደርገዋል ያሏቸውን ውጊያዎች ጨምሮ በአካባቢው በቅርብ ጊዜ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች፤ “ሰሜን ኢትዮጵያን በግጭት ውስጥ የዘፈቀ አርቆ አሳቢነት የጎደለው” እና ነገሮችን “ወደ ጦርነት የመግፋት አደገኛ አካሄድን በድጋሚ የሚያሳዩ ነው” ሲሉም በትላንቱ መልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል። 

የኮንግረስ አባሉ በትግራይ እየተባባሰ መጥቷል ላሉት ውጊያ፤ በማስረጃነት የጠቀሱት በክልሉ “በቅርቡ የተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶችን” ነው። የዴሞክራቶች ተወካዩ “ታጣቂ ቡድኖች በክልሉ እና በአካባቢው በሚገኙ የጤና ማዕከላት እና የሰብአዊ ርዳታ ሠራተኞች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል” ሲሉም በመልዕክታቸው አክለዋል።   

ጥቃቶቹ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አለመዘገባቸውን በመግለጫቸው የጠቆሙት ሚክስ፤ ለዚህም “በከፍተኛ ሁኔታ የተገደበ” ያሉት የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት አስተዋጽዖ እንዳበረከተ አክለዋል። የኮንግረስ አባሉ “ሁሉም አካላት ለቀጠናዊ ሰላም የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ” ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)