የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ፣ አክሱም እና ሽረ ሊያደርጋቸው የነበራቸውን በረራዎች ሰረዘ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ፣ አክሱም እና ሽረ ከተሞች በዛሬው ዕለት ሊያደርጋቸው የነበራቸውን በረራዎች ሰረዘ። በመቐለ ከተማ የሚገኘውን የአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያን የትግራይ ኃይሎች መቆጣጠራቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ እና ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 13፤ 2019 ሊደረጉ ታቅደው የነበሩ በረራዎች ስድስት ነበሩ። እነዚህ በረራዎች መሰረዛቸውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኃላፊነት ደረጃ የሚሰሩ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

በመቐለ ከተማ የሚገኙ ሁለት ነዋሪዎችም ዛሬ ጠዋት ወደ ከተማው የመጣ አውሮፕላን እንደሌለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሌላ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በመቐለ ከተማ “አብርሃ ካስትል” አካባቢ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትኬት መሸጫ ቢሮ ዛሬ ጠዋት በሄዱበት ወቅት፤ “ለጊዜ በረራ ተቋርጧል። በቀጣይ እናሳውቃለን” መባላቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትኬት መቁረጫ ድረ ገጽ፤ ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ እና ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ በዛሬው ዕለት ሊደረጉ የነበሩ በረራዎች “ፕሮግራም እንዳልተያዘላቸው” በዝርዝሩ ላይ አመልክቷል። ከነገ ሐሙስ እስከ መጪው ቅዳሜ ድረስ ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ መጓዝ የሚፈልጉ መንገደኞች ግን በአየር መንገዱ ድረ ገጽ ላይ አሁንም ትኬት መቁረጥ እንደሚችሉ ይታያል። 

በአየር መንገዱ ድረ ገጽ መረጃ መሰረት፤ በቀጣዩቹ ሁለት ቀናት ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ሊደረጉ የታቀዱ በረራዎች ትኬት ግን “ሙሉ ለሙሉ ተሽጠው” አልቀዋል። በትኬት መቁረጫው ድረ ገጽ፤ ከአዲስ አበባ ወደ አክሱም እና ሽረ በዛሬው ዕለት ሊደረጉ ታቅደው የነበሩ ሁሉም በረራዎች እንደ መቐለው ሁሉ “ፕሮግራም አልተያዘላቸውም” የሚል መልዕክት አስፍሮባቸዋል። 

ወደ ሁለቱ ከተሞች ዛሬ ረቡዕ ሊደረጉ የነነበሩ በረራዎች መሰረዛቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተመሳሳይ መልኩ ወደ መቐለ፣ አክሱም እና ሽረ የሚደረጉ በረራዎችን ለመጨረሻ ጊዜ ያቋረጠው ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ነበር።

አየር መንገዱ ወደ ሶስቱ ከተሞች አቋርጧቸው የነበሩ በረራዎቹን፤ ከአምስት ቀናት በኋላ ዳግም መጀመሩም ይታወሳል። የዛሬው የበረራ መሰረዝ ለምን ያህል ቀን እንደሚቀጥል፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]