በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሌራ ወረርሽኝ “ዳግም ሊከሰት” የሚችልባቸው ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ   

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በቀጣዩቹ ቀናት እንደሚጨምር በሚጠበቀው የዝናብ ሁኔታ ሳቢያ የኮሌራ ወረርሽኝ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ። በክልሉ “ሁሉም አካባቢዎች” ይህንኑ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ “የመከላከል እና የዝግጁነት ስራ” እንዲጠናከርም ኢንስቲትዩቱ መልዕክት አስተላልፏል።

ተቋሙ የኮሌራ ወረረሽኝ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክቱን ያስተላለፈው፤ በክልሉ ስር ለሚገኙ 12 ዞኖች ጤና መምሪያዎች እንዲሁም ለሶዶ፣ ዲላ እና አርባ ምንጭ ከተሞች በጻፈው ደብዳቤ ነው። ባለፈው አርብ መስከረም 8፤ 2019 የተጻፈው ይህ ደብዳቤ፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከዓመታት በፊት የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ፤ “ቀላል የማይባል” ህመም እና ሞት ማስከተሉን አስታውሷል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሁኑ ወቅት የኮሌራ ወረረሽኝ “በየትኛውም አካባቢ” ያልተከሰተ መሆኑንም የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በደብዳቤው ጠቅሷል። ሆኖም ለበሽታው መከሰት “ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠር”፤ ወረረሽኙ “ዳግም ሊከሰት የሚችልበት” አጋጣሚዎች እንዳሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።

ተቋሙ ለዚህ በማስረጃነት ያቀረበው፤ በኢል-ኒኖ የአየር ንብረት ክስተት ምክንያት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የዝናብ ሁኔታ እንደሚጨምር የሚቴዎሮሎጂ የትንበያ መረጃዎች ማመልከታቸውን ነው። የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከትላንት በስቲያ ያወጣው መረጃም ይህንኑ አስተጋብቷል።

በኮሚሽኑ መረጃ መሰረት፤ ኤል-ኒኖ በ37 ዞኖች ስር በሚገኙ 178 ወረዳዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በትንበያዎች ተደርሶበታል። ኤል-ኒኖ በተለያዩ ሀገራት ድርቅ፣ ጎርፍና ሌሎች አደጋዎችን ሊያስከትል የሚችል ተጽዕኖ እንዳለው የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስገንዝቧል። 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኤል-ኒኖ ሳቢያ የሚጨምረውን ዝናብ ተከትሎ የሚፈጠረው ጎርፍ፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃን በቀላሉ በመበከል ለኮሌራ ወረርሽኝ “ማገርሸት ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር” እንደሚችል የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በደብዳቤው አስረድቷል። ኢንስቲትዩቱ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ “የመከላከል እና የዝግጁነት ስራ” በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲጠናከርም በደብዳቤው አሳስቧል።

ደብዳቤው ከተጻፈላቸው የክልሉ ዞኖች አንዱ በሆነው በደቡብ ኦሞ፤ በግንቦት 2015 ዓ.ም. የኮሌራ ወረረሽኝ ተከስቶ ነበር። ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማስከትል፣ በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጥጦ በማስወጣት፣  አቅምን በማዳከም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)