የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና ራሳቸውን “የትግራይ ሰላም ኃይሎች” ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ትላንት ቅዳሜ ምሽት ወደ መቐለ መግባታቸውን ተከትሎ በከተማይቱ የተሻለ መረጋጋት መስፈኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች እና በስፍራው የሚገኙ ጋዜጠኞች ገለጹ። ከአርብ ምሽት ጀምሮ በመቐለ ከተማ በሚገኙ የመንግስት እና የግል ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ ሲፈጸም እንደነበር ያስረዱት የዓይን እማኞቹ፤ ትላንት ምሽትም በአንዳንድ አካባቢዎች የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል።
ዝርፊያው የተጀመረው የመቐለ ከተማን ጸጥታ ሲያስጠብቁ የቆዩ ኃይሎች፤ ከትላንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ ከተማይቱን ለቅቀው ከወጡ በኋላ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የጸጥታ ኃይሎቹ፤ ካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ወዲህ ትግራይ ክልልን የማስተዳደር ኃላፊነት ከጊዜያዊ አስተዳደር የወሰደው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሚታዘዙ ነበሩ።
እነዚህ ኃይሎች መሳሪያቸውን እንደታጠቁ እስከ ትላንት ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ በቡድን እና በግል በመቐለ ከተማ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በስፍራው የሚገኝ ጋዜጠኛ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። የጸጥታ ኃይሎቹ መቐለን ለቅቀው የወጡት በውቅሮ ከተማ አቅጣጫ እንደነበር የገለጸው ጋዜጠኛው፤ ከዚያ በኋላ በነበረው ጊዜ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች ወደ ዘረፋ መግባታቸውን አስረድቷል።



ዘረፋ ከተፈጸመባቸው የመንግስት ተቋማት መካከል “ደጀን” በመባል የሚታወቀው የትግራይ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት፣ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና ጽምፂ ወያነ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደሚገኙበት ጋዜጠኛው እና ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። በመቐለ ከተማ ስር የሚገኙ የክፍለ ከተሞች ጽህፈት ቤቶችም ተመሳሳይ የዘረፋ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው አመልክተዋል።
ይህንኑ ዘረፋ በመፍራት በከተማይቱ የሚገኙ የንግድ መደብር ባለቤቶች፤ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ጋዜጠኛው ተናግሯል። በዚሁ ቀን የሞባይል ስልክ፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የልብስ፣ የኮስሞቲክስ እና የህንጻ መሳሪያ መሸጫ ባለቤቶች፤ ንብረቶቻቸውን ከዘረፋ ለመከላከል ወደ ሌላ ቦታ ሲያሸሹ መመልከቱንም አክሏል።
በዛሬው ዕለት በመቐለ ዋና ዋና መንገዶች “የትግራይ ሰላም ኃይሎች” ጸጥታ ሲያጠብቁ ቢታዩም፤ የንግድ መደብሮች አለመከፈታቸውን ጋዜጠኛው ገልጿል። ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከመቐለ የተላኩ ፎቶግራፎች፤ አብዛኞቹ የከተማይቱ ዋና ዋና መንገዶች በጭርታ መዋጣቸውን ያሳያሉ።



በመንገዶቹ ላይ የሚታዩት ተሽከርካሪዎች ብዛትም፤ ወትሮ ከነበረው አነስተኛ መሆኑ በፎቶዎቹ ላይ ይታያል። ዛሬ እሁድ እኩለ ቀን ገደማ “የትግራይ ሰላም ኃይሎች” ታጣቂዎች እና የአፋር ክልል የጸጥታ ኃይሎች የጫኑ ፒክ አፕ መኪናዎች፤ የጡሩንባ ድምጽ እያሰሙ በመንገዶቹ ላይ ሲዘዋወሩ በስፍራው ያለ ጋዜጠኛ ተመልክቷል።
በዚህ መልኩ ደስታቸውን ሲገልጹ ከነበሩት መካከል የዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ አመራሮች እንደሚገኙበት ጋዜጠኛው ገልጿል። ከእነዚህ የስምረት ፓርቲ አመራሮች ውስጥ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ፀጋይ ገብረተኽለ አንዱ መሆናቸውን ጋዜጠኛው ተናግሯል።
በመቐለ ከተማ መንገዶች አልፎ አልፎ የሚታዩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ የመቐለ ዩኒቨርሲቲን እና ባለፉት ቀናት እንደተዘረፈ የተገለጸውን የትግራይ ሰማዕታት ሐውልት (ሐውልቲ) ማዕከልን መቆጣጠራቸውን ጋዜጠኞች እና ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የመከላከያ ሰራዊት እና “የትግራይ ሰላም ኃይሎች” ወደ መቐለ መግባት የተሻለ መረጋጋት ማምጣቱን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፤ አሁንም ግን በከተማይቱ የዘረፋ ስጋት እንዳለ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































