የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብጽ “ውጥረቶችን ይበልጥ ከሚያባብሱ” እርምጃዎች እንዲታቀቡ ጥሪ አቀረበ

በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እና በግብጽ መካከል “የጨመረውን ውጥረት” በስጋት ውስጥ ሆኖ በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ሶስቱ ሀገራት የግንኙነት መንገዶቻቸውን ጠብቀው በማቆየታቸው አስፈላጊነት ላይም አጽንኦት ሰጥቷል። 

የህብረቱ ኮሚሽን ዛሬ ሐሙስ እኩለ ለሊት ገደማ ላይ መግለጫውን ያወጣው፤ ኢትዮጵያ የኤርትራ እና የግብጽ ዲፕሎማቶች ሀገሪቱን ጥለው በ48 ሰዓት እንዲወጡ ማዘዟን ተከትሎ ነው። ኢትዮጵያ ይህንኑ ባስታወቀችበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  መግለጫ፤ በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን ገልጻለች።

ኢትዮጵያ እርምጃ መውሰዷን ካሳወቀች ከሰዓታት በኋላ ኤርትራም አጸፋዊ ምላሽ ሰጥታለች። ኤርትራ ዛሬ ምሽት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን “ማናቸውንም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከማቋረጥ ውጪ ሌላ አማራጭ የለኝም” ብላለች።

 ኤርትራን ያስቆጣት የኢትዮጵያ እርምጃ፤ ወደ ግብጽም ተሻግሯል። ይህንኑ የሚያሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ በመንግስት እና ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ባላቸው መገናኛ ብዙሃን ዛሬ ምሽት ተሰራጭቷል።

መገናኛ ብዙሃኑ ያሰራጩት ደብዳቤ፤ አንድ የግብጽ ዲፕሎማት በ48 ሰዓት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቅቆ እንዲወጣ የሚያዝ ነው።  በሶስቱ ሀገራት መካከል “የጨመረውን ውጥረት”  በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራቱ ከተጨማሪ እርምጃ ራሳቸውን እንዲቆጥቡ አሳስቧል። 

ሶስቱ ሀገራት “ውጥረቶችን ይበልጡኑ ከሚያባብሱ” እንዲሁም “የቀጠናውን ሰላም እና መረጋጋት ከሚያደፈርሱ” መግለጫዎች እንዲታቀቡም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል። ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብጽ የግንኙነት መንገዶቻቸውን ጠብቀው በማቆየታቸው አስፈላጊነት ላይም አጽንኦት ሰጥቷል። 

በአፍሪካ ህብረት የመመስረቻ ድንጋጌ መርሆዎች መሰረት፤ ሶስቱ ሀገራት “ልዩነቶቻቸውን በመደበኛ የዲፕሎማሲያዊ የግንኙነት መንገዶች እና ሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ” ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው አሳስቧል። ሃምሳ አምስት አባል ሀገራትን ያቀፈው የአፍሪካ ህብረት፤ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብጽ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚደረጉ ጥረቶችን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሀገራት በመነጋገር ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)