በትግራይ ክልላዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ፤ የፌደራል መንግስት “ሙሉ ትግራይን እንደሚያስተዳድር” አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ  

በትግራይ ክልል “ለምርጫ የሚሆን አመቺ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ” የፌደራል መንግስት “ሙሉ ትግራይን እንደሚያስተዳድር” የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። በክልሉ በፌደራል የሚመራ “ኮማንድ ፖስት” እንደሚቋቋም የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ በሁሉም ቦታዎች በሚካሄድ ምርጫ የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንደሚሰየሙ አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪነታቸው እንዲቀጥሉ በትላንትናው ዕለት በድጋሚ የተሾሙት አቶ ጌታቸው፤ የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ቲቢኤስ ከተሰኘው የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው። አንድ ሰዓት የሚጠጋ ጊዜ በወሰደው በዚህ ቃለ ምልልስ፤ አቶ ጌታቸው በትግራይ ክልል በቀጣይ የሚከናወኑ ስራዎችን በተመለከተም ጥቆማ ሰጥተዋል።

አቶ ጌታቸው ጥቆማውን የሰጡት ላለፉት ሳምንታት ሲካሄድ ከቆየ ውጊያ በኋላ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሚመሩ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የነበሩ የትግራይ ክልል በርካታ አካባቢዎች፤ በመከላከያ ሰራዊት እና አጋሮቹ መያዛቸውን ተከትሎ ነው። የትግራይ ክልል አብዛኞቹ አካባቢዎች በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፤ በክልሉ ከአሁን በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደማይኖር ይፋ አድርገዋል።

የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል “አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር” እንዲመሰረት ውሳኔ ያሳለፈው በመጋቢት 2015 ዓ.ም ነበር። ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲመሩ በዚሁ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት፤ በወቅቱ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ነበሩ። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ለሁለት ዓመት በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ ጌታቸው፤ በመጋቢት 2017 ዓ.ም ኃላፊነታቸውን ምክትላቸው ለነበሩት ለሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ አስረክበዋል። የሌተናል ጄነራል ታደሰ ኃላፊነት እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ስልጣን፤ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ወደ ስራ እንዲመለስ የተደረገው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ካካሄደው የክልል ፕሬዝዳንት ምርጫ በኋላ አክትሟል።

ከፌደራል መንግስት ይሁንታ ውጭ በ2012 ዓ.ም በትግራይ ክልል በተደረገው ምርጫ የተመረጠው የክልሉ ምክር ቤት፤ የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑትን ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን በሚያዝያ 2018 ዓ.ም. መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ መሾሙ ይታወሳል። ዶ/ር ደብረጽዮን የሚመሩት ህወሓት፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተሰጥቶት የነበረው ህጋዊ እውቅናው በግንቦት 2017 ዓ.ም. መሰረዙ አይዘነጋም።

ህወሓት በትግራይ ክልል ውጊያ እስከተቀሰቀሰበት ድረስ፤ ክልሉን ለአምስት ወራት ሲያስተዳድር ቆይቷል። ከዚህ በኋላ በትግራይ ክልል የሚኖረው አስተዳደር በምርጫ የሚመሰረት መሆኑን አቶ ጌታቸው ረዳ በትላንቱ ቃለ ምልልሳቸው ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በፌደራል መንግስት እቅድ መሰረት በመጪዎቹ ስድስት ወራት በትግራይ ምርጫ ለማካሄድ እንደታቀደ አቶ ጌታቸው ጨምረው ገልጸዋል። “ህወሓት ይዞት የነበረው ሁሉን ነገር የመቆጣጠር በሽታ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መሰበር መቻል አለበት” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በስድስት ወራት ውስጥ ለሚደረገው ምርጫ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች “እንቅስቃሴ ማድረግ” እና “ስራዎችን ማከናወን” እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል አቋቁሞት የነበረውን ጊዜያዊ አስተዳደር በዋና ስራ አስፈጻሚነት ከዚህ ቀደም የመሩት ዶ/ር አብርሃም በላይ፤ ከሳምንት በፊት ለፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ምርጫን በተመለከተ ተመሳሳይ ጥቆማ ሰጥተው ነበር። ዶ/ር አብርሃም በትግራይ “በወራት ውስጥ” ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ፤ የፌደራል መንግስት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው አመልክተዋል።

በክልሉ ስር ያሉ የቀበሌ እና የወረዳ አስተዳደሮችን የማደራጀቱ ስራ፤ “በፌደራል መንግስት ኃላፊነት ህዝቡ የሚያደራጅበት ሁኔታ ይፈጠራል” ሲሉም ዶ/ር አብርሃም አክለዋል። አቶ ጌታቸው በትላንቱ ቃለ ምልልሳቸው ይህንኑ አስተጋብተዋል።

“ህዝብ በተወካዮቹ በኩል አድርጎ በየወረዳው በየቀበሌው የዕለት ተዕለት ተግባራት በሚፈጽሙ [ተመራጮች] የሚተዳደርበት ሁኔታ ይፈጠራል። የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ። በተቀናጀ መልኩ በሁሉም ቦታዎች ምርጫ እየተካሄደ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ይኖራሉ” ሲሉ አካሄዱን አብራርተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው “ለምርጫ የሚሆን አመቺ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ የፌደራሉ መንግስት ሙሉ ትግራይን ያስተዳድራል” ሲሉም ተደምጠዋል። በትግራይ ክልል ደረጃ የሚቋቋም “ኮማንድ ፖስት” እንደሚኖር በቃለ ምልልሳቸው የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ የእዚህ መዋቅር የመጀመሪያ ስራ “ሰላም እና መረጋጋት መፍጠር” መሆኑን አስረድተዋል። 

“ህዝብ በተወካዮቹ በኩል አድርጎ በየወረዳው በየቀበሌው የዕለት ተዕለት ተግባራት በሚፈጽሙ [ተመራጮች] የሚተዳደርበት ሁኔታ ይፈጠራል። የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ። በተቀናጀ መልኩ በሁሉም ቦታዎች ምርጫ እየተካሄደ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ይኖራሉ”

የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልልን ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ “ወደ መደበኛ (normal) እንቅስቃሴ” ለመመለስ የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በትግራይ ክልልም እንዲጀመር፤ የፌደራል መንግስት ለክልሉ “ራሱን የቻለ ማርሻል ፕላን የማውጣት እቅድ እንዳለውም” ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ያሉ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራም፤ የፌደራሉ መንግስት እቅድ መሆኑ አቶ ጌታቸው አመልክተዋል። “ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ እንቅፋት ይፈጥር የነበረው ኃይል አሁን የለም። ተፈናቃዮች መመለስ አለባቸው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

“የትግራይ አጠቃላይ የግዛት arrangement ስርዓት ለማስያዝ; አሁን እንቅፋት የሚሆን ነገር የለም። ጥያቄ ያላቸው አካላት ካሉ፤ ጥያቄያቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሊያቀርቡ ይችላሉ።…በወልቃይት የማንነት ጥያቄ አለን የሚሉ አካላት ካሉ፤ ስርዓት ባለው መንገድ በሕገ መንግስቱ መሰረት ይታያል” ሲሉም በቀጣይ የሚጠበቀውን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)