የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 3፤ 2019 በወቅታዊ “የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ላይ” በዝግ ሊመክር ነው። የዝግ ስብሰባው የተጠራው፤ “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ መባባሱን” ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ተገልጿል።
የነገው ስብሰባው እንዲካሄድ የጠየቀችው በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ያላት ዩናይትድ ስቴትስ እንደሆነች “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁ አንድ የዲፕሎማቲክ የመረጃ ምንጭ ለመረዳት ችላለች። አስራ አምስት ሀገራትን በሚይዘው የጸጥታው ምክር ቤት፤ ከአፍሪካ በተለዋጭ አባልነት የተካተቱት የኢትዮጵያ ጎረቤት ሶማሊያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ላቤሪያ ናቸው።
በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሰው ውጊያ ሶስተኛ ሳምንቱን በሚደፍንበት ዕለት በሚካሄደው በዚህ ስብስባ፤ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፖለቲካ እና ሰላም ግንባታ ጉዳዮች ክፍል የሚጋበዙ ባለስልጣን ማብራሪያ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሰሜን ኢትዮጵያ ካለፈው መስከረም አጋማሽ ጀምሮ ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የመንግስታቱ ድርጅት ጉዳይ “እጅጉን እንዳሳሰበው” በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባለፈው አርብ በቃል አቃባያቸው በኩል ባወጡት መግለጫ፤ በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ያለው ውጊያ፤ አጠቃላይ ቀጠናውን ወደ በለጠ አለመረጋጋት ሊያሸጋግር እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር። ጉተሬዝ በዚሁ መግለጫቸው፤ “የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገብተዋል” የሚሉ ሪፖርቶች እንደሳሰቧቸውም ገልጸዋል።
ሁሉም የቀጠናው ሀገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር በተጣለባቸው ግዴታ መሰረት፤ “በማንኛውም ሀገር ግዛታዊ አንድነት ወይም ፖለቲካዊ ነጻነት ላይ ከሚሰነዘር ዛቻ ወይም የኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡም” ጉተሬዝ በመግለጫቸው አሳስበዋል። ዋና ጸሀፊው የቀጠናው ሀገራት “በሀገራት የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ያለመግባት መርህን” ማክበር እንደሚገባቸውም አስታውሰዋል።
ጉተሬዝ ይህን መግለጫ ከማውጣታቸው አንድ ቀን አስቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፤ ኤርትራ “የኢትዮጵያን ግዛት መውረሯን” አስታውቀው ነበር። ኤርትራ ወታደሮቿን በአፋጣኝ ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣ በደብዳቤያቸው የጠየቁት ዶ/ር ጌዲዮን፤ ያም የማይሆን ከሆነ “ኢትዮጵያ ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት” አስጠንቅቀዋል።
ኤርትራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኦስማን ሳሌህ በኩል ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በላከችው የምላሽ ደብዳቤ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበባትን ክስ አስተባብላለች። ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ “ጦርነት ካወጀች ሶስት ዓመት አስቆጥራለች” ስትልም ወንጅላለች።
የተመድ ዋና ጸሀፊ በባለፈው አርብ መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ ግጭት ተሳታፊ በሆኑ ወገኖች ላይ ተጽዕኖ ያላቸው ሀገራት በጉዳዩ ላይ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። እነዚህ ሀገራት ያላቸውን ተጽዕኖ በመጠቀም ግጭቱን ለማብረድ የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲደግፉ እና ሁኔታውን ሊያባብሱ የሚችሉ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ጉተሬዝ ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































