በጃዋር መሐመድ ላይ የቀረቡት ክሶች ምንድናቸው?

በተስፋለም ወልደየስ 

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአቶ ጃዋር መሐመድ እና ሌሎች 23 ተከሳሾች ላይ ዛሬ ሰኞ መስከረም 11፤ 2013 በይፋ ክስ መስርቷል። ጉዳዩ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት፤ በዛሬው ውሎው የክስ ሰነዶቹ ለተከሳሾች እና ጠበቆቻቸው እንዲከፋፈል አድርጓል። 

አቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ ላይ 10 ክሶችን የዘረዘረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አቶ ጃዋር በአራት ወንጀሎች መከሰሳቸው ተመልክቷል። ከአቶ ጃዋር ክሶች ሶስቱ እርሳቸውን ብቻ የሚመለከቱ ሲሆን አራተኛው ግን እርሳቸውን ጨምሮ 15 ተከሳሾች የተካተቱበት ነው። 

በክስ ሰነዱ በቀዳሚነት የተቀመጠው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ህግ በመተላለፍ አስራ አምስት ተከሳሾች ፈጽመውታል የተባለ ወንጀል ነው። የጦር መሳሪያ ይዞ በማመጽ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግስት ላይ ተደረገ በተባለው በዚህ ወንጀል ስር ተሳትፈዋል ከተባሉት ውስጥ፤ በክስ ሰነዱ ላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የተዘረዘሩት አቶ ጃዋር፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሀምዛ አዳነ ይገኙበታል። 

ተከሳሾቹ ሃይማኖትን እና ብሔርን መሰረት በማድረግ በተለይም በአማራ ብሔር ተወላጆች፣ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ለማድረግ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም እንዲሁም በአካል በመገኘት የእርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳታቸውን አቃቤ ህግ በክሱ አመልክቷል። ተከሳሾቹ ባነሳሱት ግጭት ምክንያትም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ከተሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ የሰው ህይወት መጥፋቱን እና ንብረት መውደሙንም ገልጿል።

አቃቤ ህግ በኦሮሚያ ክልል ነበሩ ባላቸው ግጭቶች የ167 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና 360 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን በክስ ሰነዱ ጠቅሷል። በእነዚሁ ግጭቶች ግምቱ 4.7 ቢሊዮን ብር ገደማ የሆነ የመንግስት እና የግለሰቦች ንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን ጠቅሶ ተከሳሾቹን ለዚህ ጉዳት ተጠያቂ አድርጓቸዋል። 

በተመሳሳይ ሁኔታ ተከሳሾቹ ባነሳሱት ግጭት ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የ13 ሰው ህይወት ማለፉን እና 48 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመት የመንግስት እና የግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም አቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ ላይ አስፍሯል። በዚህም በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተላቸውን አብራርቷል። 

በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው እና በአቶ ጃዋር ላይ ብቻ የቀረበው ሌላኛው ክስ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ማቀድ እና መሰናዳት ወንጀል ነው። ተከሳሹ “የተለያዩ ግድያዎችን በተለያዩ ሰዎች ላይ ሊፈጽሙ የሚችሉ እያንዳንዳቸው አስር አባላት ያሏቸው፣ በህቡዕ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ በርካታ አደረጃጀቶች ፈጥሮ ሲመራ እና ዝግጅት ሲያደርግ የነበረ በመሆኑ” በዚህ ወንጀል መከሰሱን አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ገልጿል።

በክስ ዝርዝሩ ላይ በአራተኛነት የተቀመጠው ወንጀልም አቶ ጃዋርን ብቻ የሚመለከት ነው። የቴሌኮም ማጭበርበው አዋጅ ስር ያለ ድንጋጌን በመተላለፍ የቀረበው ይህ ክስ፤ ተከሳሹ “የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጀቱ ከዘረጋው ውጪ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዘርግተዋል” ሲል ይከስሳል።  

አቶ ጃዋር “ከኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ፍቃድ ሳይኖራቸው፣ ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሰረት ልማት ወደ ጎን በመተው፣ በግለሰብ ደረጃ መያዝ እና መጠቀም የማይፈቀደውን ሮኬት ፕሪዝም ጂን 2 ሲስተም፣ ከሳተላይት የሚመጣውን ሲግናል ለመሰብሰብ እና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቪሳት ሳህን እንዲሁም ዩቢኪውቲ ኤጅ ራውተር የሆኑ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ከአሜሪካን ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተዋል” ሲል ክሱ ያብራራል። 

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለብቻቸው የተከሰሱት አቶ ሚሻ አደም፤ እነዚህን የቴሌኮም መሳሪያዎች በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ፤ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የአቶ ጃዋር ቤት መግጠማቸውን ክሱ ይጠቅሳል። በክሱ ላይ የጃዋር ግብረአበር እንደሆነ የተገለጹት አቶ ሚሻ፤ በሞባይል ስልክ ቀፎዎች፣ ታብሌቶች ወይም ኮምፒውተሮች አማካኝነት የረዥም ርቀት ግንኙነት ማድረግ የሚያስችል የኔትወርክ ሲስተም መዘርጋታቸውም ተመልክቷል። 

በቤት ውስጥ በተዘረጋው መሳሪያ አማካኝነትም የግል ኔትወርክ ሲስተም እንዲኖር በማድረግ የተለያዩ የዳታ፣ የድምጽ፣ የቪዲዩ እና ሌሎች ግንኙነቶችን በማድረግ እና ኔትወርኩን በመጠቀም ዕቃዎችን መቆጣጠር መቻላቸውም በክሱ ሰፍሯል። ተከሳሹ በህግ ለግለሰብ የማይፈቀደውን የቴሌኮም መሰረተ ልማት የዘረጋ በመሆኑ መከሰሱም በክሱ ተገልጿል።

“ለሁለተኛ ጊዜ በአሸባሪነት በመከሰሴ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል”

– አቶ ጃዋር መሐመድ

አቶ ጃዋር ለብቻቸው የተከሰሱበት የመጨረሻው ወንጀል በሰነዱ ላይ በአምስተኛ ክስነት የቀረበ ነው። ተከሳሹ የጸና ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ መያዝ ወይም ማስቀመጥ ወንጀል መፈጸማቸውን የአቃቤ ህግ ክስ ያሳያል። በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ 01፣ ልዩ ቦታው ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የተከሳሽ መኖሪያ ቤት፤ ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ በተደረገ ብርበራ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ መገኘቱ ለዚህ ወንጀል በማስረጃነት ቀርቧል። ተከሳሹ በወቅቱ 19 የሽጉጥ ጥይቶች ቤታቸው ውስጥ አስቀምጠው መገኘቱም በክሱ ተጠቅሷል። 

የቀረበባቸውን ክስ “ድራማ” ሲሉ ያጣጣሉት አቶ ጃዋር፤ እርሳቸውም ሆነ ሌሎች የተከሰሱት ወንጀል ሰርተው ሳይሆን “ከምርጫ ለማስወጣት” እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ባስተላለፉት አጭር መልዕክት ተናግረዋል። ይህ ደግሞ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በአቶ እስክንድር ነጋ እና በአቶ ልደቱ አያሌው ላይ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል። ኦነግን ለመከፋፈል የሚደረገው ጥረትም ገዢው ፓርቲ ተቀናቃኞቹን “ከምርጫ ሜዳ ለማውጣት የሚያደርገው ነው” ብለዋል።   

“ለሁለተኛ ጊዜ በአሸባሪነት በመከሰሴ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል” ያሉት አቶ ጃዋር ወደፊትም ለብሔሮች እኩልነት መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ አምባገነናዊ ስርዓትን ለማስፈን የሚደረግ ሙከራ እና ተቃዋሚን አስሮ ለመግዛት የሚደረግ ጥረት “ተራ ህልምና ቅዥት ነው” ሲሉም አክለዋል። እንዲህ አይነት አካሄድ “ለሀገር ከፍተኛ አደጋ ነው” ያሉት ተከሳሹ መፍትሄው በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት መሆኑን በማስገንዘብ ንግግራቸውን አጠቃልለዋል። 

በዛሬው የችሎት ውሎ 18 ተከሳሾች በፍርድ ቤት የተገኙ ቢሆንም የክስ ሰነዱ በንባብ ሳይሰማ ቀርቷል። የተከሳሽ ጠበቆች፤ ቀደም ብሎ በተከፈተ ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሌላ ችሎት ቀጠሮ የነበራቸው አቶ ደጀኔ ጣፋ እና መስተዋርድ ተማም ዛሬ መቅረብ ባለመቻላቸው፤ እነርሱ ባሉበት የክስ ሰነዱ እንዲነበብ ችሎቱን ጠይቀዋል። ችሎቱ ሙሉ ክሱን በንባብ ለማሰማት ለመጪው ሐሙስ መስከረም 14፤ 2013 ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)