በሃሚድ አወል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ መተከል ዞን፤ ቡለን ወረዳ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በወረዳው የሰዓት ዕላፊ ገደብ ተጣለ። በቅዳሜው ግጭት ቢያንስ 14 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የቡለን ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በትላንትናው ዕለት ባሰራጨው “ጥብቅ ማሳሰቢያ”፤ በአካባቢው ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ድረስ ከጸጥታ ኃይሎች ውጭ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ ተከልክሏል። ከትላንት እሁድ ሐምሌ 4 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረ የተነገረውን ይህን የሰዓት ዕላፊ ገደብ የተጣለው በመተከል ዞን በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ነው።
ኮማንድ ፖስቱ ከሰዓት ዕላፊ ገደቡ በተጨማሪ ከከተፈቀደላቸው ሰዎች ውጭ ድምጽ ያለውም ሆነ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስ መከልከሉን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። ክልከላዎቹን ተላልፎ የተገኘ ግለሰብ ላይ “ህጋዊ እርምጃ” እንደሚወሰድበት ኮማንድ ፖስቱ “ጥብቅ ማሳሰቢያ” ሰጥቷል ተብሏል።
እንደ ቢሮው መግለጫ ከሆነ ኮማንድ ፖስቱ እነዚህን ክልከላዎች ያስተላለፈው፤ በቡለን ወረዳ እና አካባቢው የተከሰቱ “የጸጥታ ችግሮችን” መነሻ በማድረግ፤ ሁኔታውን ከገመገመ በኋላ ነው። ሆኖም መግለጫው በአካባቢው ተፈጠሩ የተባሉ “የጸጥታ ችግሮችን” ምንነት ሳይጠቅስ ቀርቷል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አራት የወረዳው ነዋሪዎች ግን ተፈጠረ የተባለውን የጸጥታ ችግር እና ያስከተለውን ጉዳት በዝርዝር አስረድተዋል። የጸጥታ ችግሩ የተከሰተው ባለፈው አርብ ከሰዓት፤ አንድ የአካባቢው ነዋሪ “በጉሙዝ ታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው” ይላሉ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቡለን ወረዳ ነዋሪ፤ የሟች ቤተሰቦች ወደ ቀብር እየሄዱ ባሉበት ወቅት ወደ ገበያ ከመጡ የጉሙዝ ተወላጆች ጋር ከተገናኙ በኋላ ግጭት መፈጠሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከትላንት በስቲያ በነበረው በዚህ ግጭት “ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ሰው ተገድሏል” ሲሉም አክለዋል።
በወረዳው የጸጥታ ችግር እንደነበር ያረጋገጡት አንድ የመንግስት ሰራተኛ፤ በግጭቱ 17 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የሰዓት ዕላፊ ገደቡ የተጣለውም ቅዳሜ ጠዋት ከተፈጠረው ግጭት በኋላ መሆኑንም አስረድተዋል።
በቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚሰራ የጤና ባለሙያ በበኩሉ፤ ቅዳሜ በነበረው ግጭት 14 ሰዎች መሞታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። በግጭቱ ዘጠኝ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ከእነርሱ መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሶስት ሰዎች ወደ ፓዌ አጠቃላይ ሆስፒታል “ሪፈር” መባላቸውን የጤና ባለሙያው ይገልጻል።
የወረዳው ነዋሪዎች ከቅዳሜው ግጭት በኋላ በአካባቢው በርካታ ሰዎች እየታሰሩ ነው ይላሉ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የቡለን ወረዳ ነዋሪ፤ ከ150 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በግል ስራ የሚተዳደሩት አንድ የወረዳዋ ነዋሪም “ትንኮሳ የፈጠረው ሳይሆን፤ ነዋሪው ህብረተሰብ በተለይ ወጣቱ ነው እየታሰረ ያለው” ብለዋል።
ሌላኛው የ27 ዓመት ወጣት የቡለን ወረዳ ነዋሪም “በግጭቱ ውስጥ የተሳተፈ ብቻ አይደለም እየታሰረ ያለው” ሲሉ ሃሳቡን አጠናክረዋል። “መሳሪያ ያለውን ሁሉ እያሰሩ ነው” ሲሉ የግል መሳሪያ ያላቸው ግለሰቦች የእስር ኢላማ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ታሪኩ ሙላት የተባለ ሌላ የአካባቢው ነዋሪም “ቅዳሜ ዕለት ግጭቱ ሲፈጠር መሳሪያ ይዛችሁ መጥታችኋል እየተባሉ የታሰሩ አሉ” ሲል ተናግሯል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መብራቱ አለሙ፤ እስራትን በተመለከተ የነዋሪዎቹን ሀሳብ ይጋራሉ። ከጥቃቱ በኋላ ባለፉት ሁለት ቀናት “በአካባቢው ከ30 በላይ ጠንካራ የሚባሉ አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻችንን ታስረዋል” ሲሉ የፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
“ተሃድሶ ወስደዋል የተባሉ ሽፍቶች፤ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ጽፈው ለኮማንድ ፖስቱ በመስጠት እንዲታሰሩ አድርገዋል” ሲሉ የሚከሱት ዶ/ር መብራቱ፤ ስም ዝርዝሩ ውስጥ የፓርቲያቸው አባሎች እና ደጋፊዎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል። “የፌደራል መንግስት ጣልቃ ካልገባ ችግሩ እዚያ ባለው የክልሉ መንግስት እና በኮማንድ ፖስቱ ይፈታል የሚል እምነት የለንም” በማለትም በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አሳሳቢነት ገልጸዋል።
“የእኛን ፓርቲ ይደግፋሉ የሚሏቸውን እየመረጡ ማሰር ተያይዘውታል። ይህን እየሰራ ያለው የዞኑ መንግስት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት እና ምርጫውን በማስፈራራት ለማለፍ የሚደረግ ጥረት ታክሎበታል” ሲሉ የአባሎቻቸው እስር ከቅዳሜው ክስተት ባለፈ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መሆኑን ተናግረዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የመተከል ዞን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጷጉሜ 1፤ 2013 ምርጫ እንዲካሄድባቸው ከወሰነባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።
በቡለን ወረዳ የተፈጠረውን ግጭት፣ ስለተጣለው የሰዓት ዕላፊ እና ታስረዋል የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎችን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የቡለን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ግዛቱ ነሲ፤ “ማብራሪያ መስጠት የሚችለው ኮማንድ ፖስቱ ነው። እኔ ስልጣን የለኝም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮምዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነም፤ “መረጃ የለኝም። በዋናነት ኮማንድ ፖስቱ ነው መረጃ የሚሰጠው” ሲሉ እንደ ወረዳ አስተዳዳሪው ሁሉ ጉዳዩን ወደ ኮማንድ ፖስቱ መርተውታል።
የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮን በስልክ አግኝተን ለማናገር ያደረግነው ጥረት፤ ጄነራሉ “ስብሰባ ላይ ነኝ” በማለታቸው ሊሳካ አልቻለም። ከእርሳቸው በተጨማሪም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ እና የመተከል ዞን የስራ ኃላፊዎች ስልኮቻቸውን ባለማንሳታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)