በአማራ ክልል ያለው “ግጭት እና ደም መፋሰስ” “በአስቸኳይ” እንዲቆም በድጋሚ የተመረጡት ርዕሰ መስተዳድር ጥሪ አቀረቡ 

በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው “ግጭት እና ደም መፋሰስ” “በአስቸኳይ” እንዲቆም፤ በክልሉ ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አቶ አረጋ ከበደ ጥሪ አቀረቡ። በዛሬው ዕለት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በድጋሚ የተመረጡት አቶ አረጋ “በጫካ የሚገኙ” ላሏቸው ታጣቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት፤  የኢትዮጵያ እና የአማራ ክልል “ህዝብ ጠላት ከሆኑ ኃይላት ጋር መተባበር በታሪክ ፊት የሚያዋርድ [ነው]” ብለዋል።

አቶ አረጋ ይህን የተናገሩት፤ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 21፤ 2019 በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ንግግራቸው፤ በክልሉ መሳሪያ ያነሱ ታጣቂዎች “ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች” “ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኘው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት” እንደሆነ አመልክተዋል።

በክልሉ ውስጥ “ያሉ ልዩነቶችን በሰላማዊ እና ፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት” አስተዳደራቸው የሚከተለውን መንገድም አቶ አረጋ በንግግራቸው ጠቁመዋል። አዲሱ የክልሉ መንግስት “የሃሳብ እና የጥቅም ልዩነቶች ያላቸው አካላት እና የፖለቲካ ኃይሎች” “በዲሞክራሲ መንገድ የሚሳተፉበትን” አሰራር እንደሚዘረጋም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።  

አቶ አረጋ ይዘረጋል ያሉት አሰራር “የተፎካካሪዎችን እና የሲቪል ማህበራትን ሚና የሚያስከብር” እንዲሁም “የመንግስትን ቅቡልነት የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል” እንደሚሆን ገልጸዋል። በዛሬው ዕለት የተመሰረተው የአማራ ክልል መንግስት ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ፤ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች “ዘላቂ ሰላም ማስፈን” መሆኑንም አቶ አረጋ ጠቁመዋል። 

የአማራ ክልል የጸጥታ እና የፍትህ አካላት እንዲሁም ተቋማት፤ “የዜጎችን ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ” እንዲችሉ” ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ” እንዲሆኑ ለማድረግ መንግስታቸው “በልዩ ትኩረት” እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። የመንግስታቸው ትኩረት እነዚህ ተቋማት “በህግ መሰረት ህዝብን የሚያገለግሉ እና ለህግ የቆሙ ሙያዊ ተቋማት እንዲገነቡ” ማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል።

በአማራ ክልል እና አጎራባች ክልሎች ያለውን “አብሮ የመኖር እና አብሮ የመልማት ባህል ለማጠናከር” መንግስታቸው ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደውንም ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው አንስተዋል። “የጥላቻ ንግግሮችን እና የሀሰት መረጃዎችን የሚመክት የኮሚዩኒኬሽን ስትራቴጂ በመንደፍ፣ የጋራ ጥቅሞቻችን እና ታሪካዊ ትስስሮቻችንን መሰረት በማድረግ፣ በተለይም ደግሞ በጋራ አብሮነታችን ላይ መሰረት በማድረግ የገዢ ትርክት ለመገንባት አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል” ብለዋል አቶ አረጋ።


ከነሐሴ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልልን ሲያስተዳድሩ የቆዩት አቶ አረጋ፤ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንዲቀጥሉ “በተባበረ ድምጽ” ይሁንታውን የሰጣቸው የክልሉ ምክር ቤት ነው። በዛሬው መስራች ጉባኤ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት አባላት ይሁንታቸውን የገለጹት፤ እጅ በማውጣት እና ጭብጨባ በተቀላቀለበት የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ነበር።  

አቶ አረጋ የአማራ ክልልን የመምራት ኃላፊነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተረከቡት፤ ከሶስት ዓመት በፊት በተካሄደ የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ነበር። አቶ አረጋ ርዕሰ መስተዳድር ተደርገው የተሾሙት፤ የአማራ ክልል በጸጥታ መደፍረስ እየታመሰ ባለበት ወቅት ነበር።

ከአራት ዓመታት በፊት በአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ የሚሊሺያ ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት እንዲመሩ ተሹመው የነበሩት አቶ አረጋ፤ በስልጣን ላይ በቆዩበት ዘመን በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ውጊያዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። 

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በልማት አስተዳደር የሰሩት አቶ አረጋ፤ ወደ ክልል የኃላፊነት ቦታ የመጡት፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ረዳት የህዝብ ተሳትፎ አማካሪ በመሆን ነው። በቀጣይነት የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሰሩት አቶ አረጋ፤ በክልሉ ሚሊሺያ ጽህፈት ቤት ለአንድ ዓመት ቆይተዋል። 

በሐምሌ 2012 የአማራ ክልል ቴክኒክ ሙያ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮን በኃላፊነት እንዲመሩ የተዛወሩት አቶ አረጋ፤ ከሁለት ዓመት በኋል የክልሉ የስራ ፈጠራ እና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። አቶ አረጋ የአማራ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት፤ የእዚሁ ቢሮ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ በነበሩበት ወቅት ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)