ኢትዮጵያ በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን እንዲዘጋ መወሰኗን አስታወቀች። በአዲስ አበባ የሚገኙ 10 ኤርትራውያን ዲፕሎማቶችም፤ በ48 ሰዓት ኢትዮጵያን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ለኤርትራ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ላልሆኑ “ጠብ ጫሪነት” እና “ትንኮሳ” ምላሽ ለመስጠት ነው። ይህን ተከትሎም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ላይ ስጋት በሚደቅኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሰማርተዋል” ባላቸው ኤርትራውያን ዲፕሎማቶች ላይ ከሀገር የማባረር እርምጃ ወስዷል።
በዚህ እርምጃ መሰረት፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሀገሪቱ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቅቀው መውጣት ይጠበቅባቸዋል። ኢትዮጵያ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን ከማባረር በተጨማሪ ለኤርትራ መንግስትም ማሳሰቢያ ሰጥታለች።

“የኤርትራ መንግስት በሉዓላዊ ሀገራት መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ከሚመሩ መርሆዎች ጋር የሚቃረኑ ማናቸውንም ድርጊቶች እንዲያቆም ኢትዮጵያ ታሳስባለች” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ አስፍሯል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን “ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የህዝብ ለህዝብ ቁርኝት” “ጠንካራ” ሲል የገለጸው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ሀገሪቱ ለእነዚህ “ከፍተኛ ቦታ የምትሰጥ” መሆኑንም አስገንዝቧል።
ኢትዮጵያ “በሰላም አብሮ ለመኖር፣ ለቀጠናዊ መረጋጋት እና ትስስር” ያለማሰለስ “ቅድሚያ ስትሰጥ” መቆየቷን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውሷል። ሀገሪቱ “አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት”፤ አሁንም ቁርጠኝነቱ ያላት መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በአፍሪካ ቀንድ “ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት እና ቀጠናዊ ትስስር” ለማረጋገጥ፤ ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገራት ጋር እንደምትሰራም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ አስፍሯል። ኤርትራ “በቀጠናው አለመረጋጋት” እንዲኖር የሚያደርጉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች እንደሆነ፤ በኢትዮጵያ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል።
ሀገሪቱ ከግብጽ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላሉ ታጣቂ ኃይሎች ድጋፍ እየሰጠች እንደሆነ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከሳምንት በፊት ለመንግስታዊው “ፐልስ ኦፍ አፍሪካ” በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ወንጅለው ነበር። የዛሬው የኢትዮጵያ እርምጃ ይፋ ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ ኤርትራ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በኩል ባወጣችው መግለጫ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን “ማናቸውንም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከማቋረጥ ውጪ ሌላ አማራጭ” እንደሌላት አስታወቃለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]


































