ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር “በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ስለበረታው ውጥረት” በዛሬው ዕለት በስልክ የተነጋገሩት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ “በሁሉም ወገኖች በኩል ውጥረት ማርገብን እደግፋለሁ” አሉ። በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሁሉም ሀገራት፤ “ድንበር ተሻጋሪ ወረራዎችን ማስወገድ ይገባቸዋል” ሲሉም አሳስበዋል።
ማርኮ ሩቢዮ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ያደረጉትን ውይይት በማስመልከት አጠር ያለ ማብራሪያ የተሰጠው፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት በኩል ነው። ጽህፈት ቤቱ ማብራሪያውን ከማውጣቱ አስቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሩቢዮ በስልክ መነጋገራቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስለ ውይይቱ ባወጣው መግለጫ፤ የዛሬው የስልክ ንግግር ያተኮረው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል እየጨመረ ስለመጣው ውጥረት እንደሆነ ገልጿል። ሁለቱ ሀገራት ላለባቸው “ውስጣዊ እና ውጫዊ ውጥረቶች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው” በ2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በተፈረመው “የሰላም ማዕቀፍ” አማካኝነት እንደሆነ ማርኮ ሩቢዮ ማሳሰባቸውን መስሪያ ቤታቸው አስታውቋል።

ለውጥረቶቹ ዘላቂ መፍትሔው የሚመጣው፤ ሁለቱ ሀገራት በሚያደርጉት “ውይይት እና ግንኙነት” እንደሆነ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። የአፍሪካ ቀንድ “ተጨማሪ ግጭቶችን መሸከም አይችልም” የሚል አቋም ያላቸው ማርኮ ሩቢዮ፤ በቀጠናው የሚገኙ ሁሉም ሀገራት “የጎረቤቶቻቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲያከብሩ” አሳስበዋል።
የቀጠናው ሀገራት “ድንበር ተሻጋሪ ወረራዎችን” ማስወገድ እንደሚገባቸውም የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዛሬው የስልክ ውይይት ላይ ማስገንዘባቸውም ተጠቅሷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በበኩላቸው የዛሬው የስልክ ውይይት ያጠነጠነው “በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የጋራ ትኩረትን በሚሹ ጉዳዮች ላይ” እንደሆነ በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።
“ያካሄድነው ውይይት በኢትዮጵያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን እድሜ ጠገብ ወዳጅነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊና ተግባራዊ አጋርነት ለማሳደግ፤ በሁለቱም ሀገራት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጫ ነው” ብለዋል አብይ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬውን የስልክ ንግግር “እጅግ ፍሬያማ” ሲሉም ገልጸውታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































