የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበር፤ በአዲስ አበባ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በተገናኙ ማግስት፤ በኢትዮጵያ እና በአጠቃላይ በቀጠናው ሁኔታ ላይ ለህብረቱ አባል ሀገራት ማብራሪያ አቀረቡ። ዲፕሎማቷ ማብራሪያውን የህብረቱ ምክር ቤት መቀመጫ በሆነችው ብራስልስ የሰጡት፤ “በቀጥታ ከአውሮፕላን እንደ ወረዱ” እንደሆነ ገልጸዋል።
ማብራሪያቸውን ያደመጠው የህብረቱ የሰላም እና ጸጥታ ኮሚቴ፤ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት አምባሳደሮች የተካተቱበት ነው። በአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና የጸጥታ ፖሊሲ ኃላፊ ካያ ካላስ ተወካይ የሚመራው ይህ ኮሚቴ፤ በህብረቱ የጋራ የውጭ እና የጸጥታ ፖሊሲ ስር በሚሸፈኑ አካባቢዎች ያለውን ዓለም አቀፍ ሁኔታ ይከታተላል።
ይህን የህብረቱን ፖሊሲ በመቅረጽ እና በተግባር ላይ በማዋል ረገድ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ኮሚቴው የኢትዮጵያ ጉዳይን ለማድመጥ የተሰበሰበው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ላይ በዝግ በመከረ በሰዓታት ልዩነት ነው።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባውን ያካሄደው፤ “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ መባባሱን” ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ተገልጾ ነበር። ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለስብሰባ ሲቀመጥ የትላንትናው በሁለት ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለአውሮፓ ህብረት የሰላም እና ጸጥታ ኮሚቴ ማብራሪያ ያቀረቡት አኔት ዌበር፤ ወደ ብራስልስ ከማምራታቸው በፊት በአዲስ አበባ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ተገናኝተው ነበር። አኔት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪን ያነጋገሩት፤ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ከሆኑት ሶፊ ፍሮም ኤመስበርገር ጋር በመሆን ነው።
ባለፈው እሁድ መቐለ እና አዲግራት ከተሞችን ጎብኝተው የተመለሱት አቶ ጌታቸው፤ ከሁለቱ ዲፕሎማቶች ጋር ያደረጉት ውይይት በትግራይ፣ በኤርትራ እና ሱዳን ጉዳዮች ላይ በተለይ ያጠነጠነ እንደነበር በይፋዊ የኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ቀጠና “ሰላም እና መረጋጋት ወሳኝ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ” ግልጽ ውይይት ማድረጋቸውን አቶ ጌታቸው በዚሁ መልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል። አቶ ጌታቸው “የአስመራ አገዛዝ” ሲሉ የጠሩት የኤርትራ መንግስት እና “ደጋፊዎቹ” ፤ “ቀጠናውን ለማናጋት” እያደረጉት ስላሉት እንቅስቃሴ ለሁለቱ ዲፕሎማቶች ማብራራታቸውን አመልክተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካሪ “በአስመራው አገዛዝ ላይ በጊዜው እርምጃ አለመውሰድ ስለሚያስከትለው አደገኛ መዘዝ” ለአውሮፓያኑ ዲፕሎማቶች ማስገንዘባቸውንም በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል። አቶ ጌታቸው ከሁለቱ ዲፕሎማቶች ጋር “መረጃ መለዋወጥ ለመቀጠል” እንዲሁም በቀጠናው የረበበው ውጥረት “የበለጠ እንዳይባባስ” በቅርበት ለመስራት መስማማታቸውንም ጠቁመዋል።
ከሰኔ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ልዩ ልዑክ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት አኔት ዌበር የአዲስ አበባ ጉዞ፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የበረታውን ውጥረት ለማርገብ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርገው ግፊት አካል ነው። በአውሮፓ ግንባር ቀደም የአፍሪካ ቀንድ ባለሙያ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጀርመናዊቷ ዲፕሎማት፤ የቀጠናውን ቀውስ በድርድር ለመፍታት ለሚደረጉ ጥረቶች እንግዳ አይደሉም።

አኔት ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም. የተደረገው የትግራይ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ በተፈረመ የግጭት የማቆም ስምምነት እንዲገታ ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ ዲፕሎማቶች መካከል አንዷ ናቸው። ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል አለመተማመን በበረታበት ወቅት፤ ዲፕሎማቷ በአዲስ አበባ እና በመቐለ ከተሞች እየተመላለሱ ባለስልጣናትን አነጋግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት የልዩ ልዑክነት ተልዕኮአቸውን እስከ ነሐሴ 2019 ዓ.ም ያራዘመላቸው አኔት፤ የሱዳን ጦርነትን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ውስጥም ከፍተኛ ሚና አላቸው። የ25 ዓመታት የስራ ልምድ ያላቸው አኔት፤ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረትን እና የጀርመን መንግስትን በአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባህር ጉዳዮች ላይ ሲያማክሩ የቆዩ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































