በሀገራት ዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ድርድር ለሚሳተፉ አማካሪዎች የሚከፈለው የገንዘብ መጠን ጣሪያ እንዲበጅለት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ጠየቁ

በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ በሚደረግ ድርድር ውስጥ የሚሳተፉ አማካሪዎች ክፍያ ላይ “አስቀድሞ ጣሪያ” እንዲበጅ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ጥሪ አቀረቡ። ዶ/ር እዮብ ሂደቱ “የተሻለ የአበዳሪዎች ቅንጅት” እንደሚያስፈልገው ጥሪ ማቅረባቸውንም ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይህን ጥሪ ያቀረቡት፤ በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የመንግስታት ዕዳን አስመልክቶ በመከረ ስብሰባ ላይ ነው። የዶ/ር እዮብ ጥሪ የተደመጠው፤ ላለፉት አምስት ገደማ ዓመታት ሲጓተት የቆየው የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ወደ መቋጫው በተቃረበበት ወቅት ነው። 

የኢትዮጵያ መንግስት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ሂደት የጀመረው በጥር 2013 ዓ.ም. ነበር። ኢትዮጵያን መሰል ሀገራት ከአበዳሪዎቻቸው ጋር ለሚያደርጉት ውስብስብ ድርድር፤ በመስኩ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የህግ እና የፋይናንስ ድርጅቶችን በአማካሪነት መቅጠር ይጠበቅባቸዋል።

ተበዳሪ ሀገራት ከሚቀጥሯቸው አማካሪዎች ጋር በመሆን የዕዳ ሽግሽግ “ስትራቴጂ” መንደፍ እንደሚገባቸው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያዘጋጀው ሰነድ ይመክራል። ይህ ስትራቴጂ ሀገራቱ ከበአዳሪዎቻቸው ጋር የሚደራደሩበትን ስርዓት መምረጥ፣ ሽግሽግ እንዲረግባቸው የሚፈልጓቸውን የዕዳ አይነቶች እና መጠን መለየት እንዲሁም የሚጠናቀቅበትን ጊዜ መወሰንን ያካትታል።

የኢትዮጵያ መንግስት በአማካሪነት ከቀጠራቸው አንዱ መቀመጫውን በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ያደረገው ላዛርድ የተባለ የፋይናንስ አማካሪ ኩባንያ ነው። ኩባንያው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ተመሳሳይ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ድርድር እያደረጉ ያሉትን ዛምቢያ፣ ጋና እና አርጀንቲናን የመሳሰሉ አገራትን ያማክራል።

በኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ የመንግስት ዋነኛ የህግ አማካሪ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ደግሞ ዋይት ኤንድ ኬዝ የተባለው ዓለም አቀፍ የህግ አማካሪ ድርጅት ነው። ፈረንሳይ እና ቻይናን ከመሳሰሉ ሀገራት፣ ከግል አበዳሪዎች እንዲሁም ዓለም ባንክን ከመሳሰሉ ባለ ብዙ ወገን ተቋማት ጋር የሚደረገው ድርድር፤ የዕዳ ቅናሽ ወለድ እና የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያን የሚያካትት ነው።

በእነዚህ ድርድሮች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ለአማካሪዎቻቸው ከሚከፍሉት በተጨማሪ የአበዳሪዎቻቸውን ወጪ እንዲሸፍኑ ይገደዳሉ። ኢትዮጵያ ለምሳሌ ከዕዳ አከፋፈል ሽግሽጉ ጋር በተያያዘ የግል አበዳሪዎችን ለሚወክል ጊዜያዊ ኮሚቴ “የተወሰኑ ክፍያዎች እና ወጪዎች” ካሳ ለመክፈል እንደተስማማች ገንዘብ ሚኒስቴር በሐምሌ 2018 ዓ.ም. አስታውቋል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፤ ይህ ካሳ የቦንድ ባለቤቶችን ለሚወክለው ጊዜያዊ ኮሚቴ የሚከፈል የ10 ሚሊዮን ዶላር “የስራ ክፍያን” ያካትታል። የጊዜያዊ ኮሚቴው የአማካሪ ክፍያ እና ወጪ፤ ከማካካሻ ክፍያው ላይ በተመጣጣኝ ሁኔታ እንደሚቀነስ ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት መድረሳቸውንም የገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ ይፋ አድርጎ ነበር።

ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ የገባችበት የቡድን 20 ማዕቀፍ፤ ተበዳሪ መንግስታት ወይም አበዳሪ ኮሚቴዎች ለሚቀጥሯቸው የፋይናንስ፣ የህግ እና የቴክኒክ አማካሪዎች፤ ወጥ የሆነ እና አስገዳጅ የክፍያ ስርዓት ወይም የክፍያ ጣሪያ የለውም። በባንኮክ በዕዳ ጉዳይ ላይ ባተኮረው ስብሰባ የኢትዮጵያን ልምድ ያካፈሉት ዶ/ር እዮብ፤ የአማካሪዎች ክፍያ አስቀድሞ ጣሪያ ሊበጅለት እንደሚገባ መናገራቸውን ብሔራዊ ባንክ በኤክስ ገጹ በኩል ባወጣው አጭር ማብራሪያ ጠቁሟል።

ዶ/ር እዮብ ወደ ብሔራዊ ባንክ ከመምጣታቸው በፊት በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታነት በሰሩባቸው ዓመታት የኢትዮጵያን የዕዳ ሽግሽግ ድርድር ጉዳይ በቀዳሚነት የያዙ ነበሩ። የብሔራዊ ባንክ ገዢው በባንኮኩ ሰብሰባ ላይ፤ በቡድን 20 ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ ለሚያመለክቱ አዳዲስ አገራት ሂደቱ “የተሳለጠ እና ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ” ያለው ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዚሁ ስብሰባ ላይ የቀረበ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ በጥሩ ሁኔታ ወደፊት እንደተራመደ አሳይቷል።  በሪፖርቱ መሰረት ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ 14 አባል አገራት መካከል፤ ከአስራ አንዱ ጋር የዕዳ አከፋፈል ሽግሽጉን የሚመለከት የሁለትዮሽ ስምምነት ተጠናቅቋል። 

ገንዘብ ሚኒስቴር እና የዩሮ ቦንድ ባለቤቶች፤ ኢትዮጵያ ያለባትን አንድ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አከፋፈል ለማሸጋሸግ ሰኔ 22፤ 2018 “በመርህ ደረጃ” ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል። ስምምነቱ ቻይና እና ፈረንሳይ በተባባሪ ሊቀ መንበርነት በሚመሩት የኢትዮጵያ ኦፊሴያል አበዳሪዎች ኮሚቴ ይሁንታ እንዳገኘ ገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

አጠቃላይ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽጉ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና ወደ መካከለኛ ደረጃ ይወርዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ ባንክ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ካለባቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ለ2019 ካጸደቀችው በጀት ውስጥ 542.1 ቢሊዮን ብር የመደበችው ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ዕዳ ክፍያ እንዲውል ነው።

ሀገሪቱ ከ2018 በጀቷ ውስጥ 24 በመቶ ገደማ ያህሉን ለዕዳ ክፍያ አውላ ነበር። ከኢትዮጵያ 2017 ረቂቅ በጀት ውስጥ ለዕዳ መክፈያ እንዲውል ተመድቦ የነበረው የገንዘብ መጠን 139.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)