በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ዳንጉር ወረዳ በትላንትናው ዕለት በተፈጸመ ጥቃት፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አምቡላንስ አሽከርካሪ የነበረው አቶ ሙሉጌታ አንዷለም መገደሉን የግብረ ሰናይ ድርጅቱ አስታወቀ። የአምቡላንሱ አሽከርካሪ የተገደለው “በታጠቁ ኃይሎች” መሆኑን ማህበሩ ጨምሮ ገልጿል።
እነዚህ ኃይሎች በቀይ መስቀል አምቡላንስ ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት፤ ትላንት ረቡዕ ጥቅምት 4፤ 2019 ከቀኑ 7 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ገደማ እንደሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል። ጥቃቱ የተፈጸመው ከዳንጉር ወረዳ ማንቡክ ከተማ በግምት 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ጂርሴ መንደር በሚባል አካባቢ እንደሆነም ማህበሩ ጠቁሟል።
በዚሁ አካባቢ አቶ ሙሉጌታ የሚያሽከረክረው የቀይ መስቀል አምቡላንስ “በመደበኛ ሰብዓዊ ተልዕኮው ላይ” እንደነበር የገለጸው ማህበሩ፤ “በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመበት ጥቃት ህይወቱን ማጣቱን አስታውቋል። በጥቃቱ የማህበሩ አምቡላንስ “ለከፍተኛ ጉዳት በመዳረጉ ከአገልግሎት ወጪ መሆኑንም” ግብረ ሰናይ ድርጅቱ አክሏል።

በአቶ ሙሉጌታ ላይ የደረሰውን ግድያ “በጽኑ ያወገዘው” የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፤ በድርጊቱ የተሰማውን “ጥልቅ ሀዘን” ገልጿል። ጥቃቱን “አሳዛኝ” እና “የሕይወት መስዋዕትነት ያስከፈለ” ሲል በዛሬው መግለጫው የጠራው ግብረ ሰናይ ድርጅቱ፤ ድርጊቱ “በማህበሩ እና በአጠቃላይ በሰብዓዊ አገልግሎቱ ላይ የደረሰ ትልቅ ኪሳራ መሆኑን የሰው ልጆች ሁሉ በጽሞና ሊገነዘቡት [ይገባል]” ብሏል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ቶላ “ይህ እንዲህ ያለ ጭካኔ እንደገና በእኛ ላይ በመድረሱ እና ለሌሎች ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ፣ ደፋር እና የሰብዓዊ አገልግሎት ጀግና ወንድማችንን ማጣታችን ልቤን በእጅጉ ሰብሮታል” ሲሉ የሀዘን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የአምቡላንስ አሽከርካሪው “የከፈለው የላቀ መስዋዕትነት፤ የሰብዓዊነትን እና የቀይ መስቀልን ከፍተኛ ዕሴቶች የሚወክሉ ናቸው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
እርሳቸው የሚመሩት ማህበር በዛሬ መግለጫው፤ የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ አምቡላንሶች፣ የህክምና ተቋማት እና ሌሎች ለሰብዓዊ አገልግሎት የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች “በማንኛውም ጊዜ መከበር እና ከጥቃት መጠበቅ እንዳለባቸው” ሁሉም አካላት ሊረዱት የሚገባ እንደሆነ አሳስቧል። የሰብዓዊ አገልግሎት ሰራተኞችን እና ተሽከርካሪዎችን የመጠበቅ ግዴታ “በትጥቅ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖችን” ጭምር የሚመለከት እንደሆነም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግን ጠቅሶ ማህበሩ አስገንዝቧል።

በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች፤ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ የተደነገጉትን እና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ግዴታዎች “እንዲያከብሩ”፣ በሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች እና ንብረቶች ላይ “ከሚፈጸም ጥቃት እንዲታቀቡ” የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በዛሬው መግለጫው ጠይቋል። ከዚህ በተጨማሪ ማህበሩ በግጭት ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የህይወት አድን እርዳታ “ያለ እንቅፋት ማድረስ እንዲችል”፣ የሰራተኞቹ እና የንብረቶቹ ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለታጣቂ ኃይሎች ጥሪ አቅርቧል።
ታጣቂ ኃይሎች በቀይ መስቀል አምቡላንስ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት የማህበሩ ሰራተኛ ሲገደል የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም። በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ታጣቂ ኃይሎች በአማራ ክልል ምዕራብ ደንቢያ በቀይ መስቀል አምቡላንስ ላይ በፈጸሙት ጥቃት፤ የአምቡላንሱ አሽከርካሪ የነበሩት አቶ መንግስት ምንይል መገደላቸውን ማህበሩ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
በታህሳስ 2017 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን እና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በማህበሩ ሁለት አምቡላንሶች ላይ በደረሰ ጥቃት፤ የሁለቱም አምቡላንስ አሽከርካሪዎች ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸውን ማህበሩ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። በአሽከርካሪዎቹ ላይ “ጥይት በመተኮስ” ጉዳት ያደረሱት፤ “ያልታወቁ ኃይሎች” መሆናቸውን ይኸው የማህበሩ መግለጫ ጠቁሟል።
የትላንትናው የአምቡላንስ ጥቃት የተፈጸመበት የዳንጉር ወረዳ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ የጸጥታ መደፍረስ ከሚያጋጥማቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በወረዳው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች፤ በርካታ የአካባቢ ነዋሪዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































