በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፤ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየሄደ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። እስካሁን በጉባኤው የተጠናቀሩ አጀንዳዎች፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ 500 ተመካካሪዎችን ለሚይዙ 8 ቡድኖች እንደሚቀርቡ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ሐምሌ 8፤ 2018 በይፋ የተከፈተው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፤ አጠቃላይ ሂደቱ ይወስዳል ተብሎ የተገመተው ጊዜ ሶስት ሳምንት ነበር። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጉባኤውን መጀመሪያ ቀን ለማብሰር ባለፈው ሰኔ ወር በሰጠው መግለጫ ላይም፤ ይህንኑ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል።
ሆኖም ጉባኤው ሲጀመር፤ አጠቃላይ የምክክር ሂደቱ የሚወስደው ጊዜ አንድ ወር ያህል እንደሚሆን ተገልጿል። በንዑስ ቡድኖች ተከፋፍለው በስምንት ዋነኛ አጀንዳዎች ላይ ሲመካከሩ የቆዩ ተሳታፊዎች የወሰዱት ጊዜ፤ አስቀድሞ ከታሰበው “የዘገየ” እንደሆነ ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አጎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
“ባስቀመጥነው የጊዜ ሰሌዳ እየሄድን ነው የሚል እምነት የለኝም” ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ እስካሁን ያለው የጉባኤው ሂደት በጊዜ ሰሌዳው በተቀመጠው ልክ እየሄደ አለመሆኑን ገልጸዋል። ሂደቱ አስቀድሞ ከታሰበው አንጻር የመዘግየት ሁኔታዎች የገጠሙት፤ በተመካካሪዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች አከራካሪ ጉዳዮችን ያካተቱ መሆናቸውን እና ቃለ ጉባኤዎችን በጥንቃቄ የመያዝ አስፈላጊነት በመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
አቶ ሙሉጌታ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት ሐምሌ 18 መጠናቀቅ የነበረበት የ50 ቡድኖች ውይይት እስከ ሐምሌ 20 መቆየቱን ነው። የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በ50 አባላት ደረጃ ሲካሄድ የነበረውን ውይይት መቋጨት ያልቻሉ የተወሰኑ ቡድኖች፤ ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 20 እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ተኩል ድረስ ድረስ ሲወያዩ ታዝቧል።
ኮሚሽነር ሙሉጌታ “ያስቀመጥነው የጊዜ ሰሌዳ የነበረን ቢሆንም በዚያ ልክ እየሄደ ነው የሚል ግምገማ ስለሌለን፤ ባለሙያዎች ቀኖችን የሚከልሱበት አግባብ ይኖራል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል እምነት የለኝም” ሲሉ አጠቃላይ ሂደቱ ከአንድ ወር በላይም ሊወስድ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫም ይህንኑ አስተጋብተዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን በዚሁ መግለጫቸው “አንዳንድ ጊዜ ነገሮች እኛ እዚህ ባስቀመጥነው ቀን ላይሄዱ ይችላሉ” ብለዋል። “ኢትዮጵያ ይሄ ዓመታችን መጨረሻ ከመጠናቀቁ በፊት በተወሰኑ አጀንዳዎች ላይ ወደ ምክረ ሃሳብ ደርሳ፤ ለ2019 ትልቅ ብስራት እንሰማ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም የሂደቱ ጊዜ ምን ድረስ ሊጓዝ እንደሚችል አመልክተዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ዛሬ አርብ ሐምሌ 24 በሰጡት መግለጫ፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት 500 አባላት በሚይዙ ጉባኤዎች ደረጃ በአጀንዳዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ አስታውቀዋል። በስምንት ቡድኖች ተከፋፍሎ ከመጪው ሰኞ ሐምሌ 27 ጀምሮ የሚካሄደው ምክክር፤ የጉባኤው ተሳታፊዎችን “ወደ በለጠ መግባባት የሚወስዷቸው” እንደሆኑ ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናት እያንዳንዳቸው 250 የጉባኤ ተሳታፊዎችን የያዙ 16 ስልታዊ ቡድኖች፤ በአጀንዳዎች ላይ ምክክር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ተመካካሪዎቹ “የራሳቸውን አጀንዳ በሚገባ እያቀረቡ፣ የጎደለውን እያሟሉ፣ ሊያቀራርቧቸው የሚችሉ ሃሳቦችን እያካተቱ” “ብዙ ውይይት” ማድረጋቸውን ፕሮፌሰር መስፍን በዛሬው መግለጫቸው ጠቁመዋል።

በእነዚህ ውይይቶች የተጠናቀሩ አጀንዳዎች 500 አባላት ለያዙ “ዋና ቡድኖች” በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውንም ዋና ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። “ [ተመካካሪዎቹ] 10 ሆነው፣ 50 ሆነው የተወያዩባቸውን፣ በአንድ አጀንዳ ስር የሄዱበትን በሙሉ፤ 250 ሆነው ደግሞ በሚገባ ካብላሉ እና ከሄዱበት በኋላ ከዚያ በመጨረሻ የተጠናቀረውን ሂደት፣ በተወሰኑ ደረጃ የተቀራረቡበትን ሂደት ለ500 ጉባኤያቸው ያቀርባሉ” ሲሉም አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























