ሙፈሪያት ካሚል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ተመረጡ

ከዚህ ቀደም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በአፈ ጉባኤነት የመሩት ሙፈሪያት ካሚል፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ተመረጡ። ከሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነታቸው ባለፈው ሳምንት የተነሱት አቶ ደስታ ሌዳሞ ምክትል አፈ ጉባኤ ሆነዋል። 

ሙፈሪያት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤው ሆነው ከመመረጣቸው አስቀድሞ፤ ላለፉት አምስት ዓመታት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ። አዲሷ አፈ ጉባኤ ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ምክር ቤቱን በአፈ ጉባኤነት ሲመሩ የቆዩትን አቶ አገኘሁ ተሻገርን ተክተዋል።

አቶ አገኘሁ ወደ እዚህ የኃላፊነት ቦታ ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የአማራ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት የመሩ ነበሩ። የቀድሞው አፈ ጉባኤ የአማራ ክልል ከፍተኛውን ስልጣን ከማግኘታቸው አስቀድሞ በክልሉ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሰርተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የመምራት ኃላፊነት ዛሬ ሰኞ መስከረም 25፤ 2019 በተካሄደው መስራች ጉባኤ የተረከቡት ሙፈሪያት በበኩላቸው፤ አብዛኛውን የኃላፊነት ጊዜያቸው ያሳለፉት በፌደራል መስሪያ ቤቶች ነው። ሙፈሪያት ሶስት መስሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት መርተዋል።

በመጀመሪያው የሚኒስትርነት ሹመታቸው የሴቶች ጉዳዮች ሚኒስቴርን የመምራት ኃላፊነት ያገኙት ሙፈሪያት፤ በወቅቱ በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካቢኔ ወጣቷ ነበሩ። ሙፈሪያት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የስልጣን ዘመን፤ ለሀገሪቱ አዲስ የሆኑትን የሰላም ሚኒስቴር እና የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን ከምስረታቸው ጀምሮ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ምክትል የመንግስት ተጠሪ ሆነው ያገለገሉት ሙፈሪያት፤ በሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ፓርላማውን በአፈ ጉባኤነት እንዲመሩ ተሹመዋል። ይህም ሙፈሪያትን የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ አፈ ጉባኤ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)