በአዲስ አበባ እና አካባቢው ከዛሬ ጀምሮ “በየትኛውም አካባቢና ከፍታ” በረራ የሚያካሄዱ ድሮኖችን “በመጥለፍ” እና ወደ ሌላ ቦታ በመውሰድ “የማሳረፍ” እርምጃ እንደሚወስድ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ። መስሪያ ቤቱ የድሮን አብራሪዎችን “ትክክለኛ መገኛ ቦታ በመለየት” እና “በቁጥጥር ስር በማዋል” ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው፤ ከዛሬ ጀምሮ “ላልተወሰነ ጊዜ” በአዲስ አበባ እና አካባቢው ማንኛውንም አይነት ድሮን ለማብረር “ፍቃድ እንደማይሰጥ” ባስታወቀበት መግለጫው ነው፡፡ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 20፤ 2019 ማምሻውን የወጣው የመስሪያ ቤቱ መግለጫ፤ በአዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ከመከናወኑ ሁለት ቀናት በፊት የተሰጠ ነው።
በ2014 ዓ.ም የተሻሻለው የመስሪያ ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ “የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሰረተ ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደህንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስጠበቅ ኃላፊነት” ለአገልግሎቱ ይሰጣል። አገልግሎቱ ለድሮን በረራዎች ይሰጥ የነበረውን ፍቃድ “ላልተወሰነ ጊዜ” ያቋረጠው እና የበረራ ክልከላውን ተግባራዊ ያደረገው ይህንኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሆነ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




































