ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ የተደረገውን ሰባተኛውን ዙር ምርጫ ተከትሎ፤ የክልል ምክር ቤቶች መስራች ጉባኤያቸውን ማካሄድ ጀምረዋል። በዚህ ረገድ ቀዳሚ የሆነው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) ነው። ትላንት ሰኞ መስከረም 18 በአዳማ ከተማ ጉባኤውን ያደረገው ምክር ቤቱ፤ የክልሉን ፕሬዝዳንት እና ምክትሎቻቸውን በመምረጥ የአዲስ መንግስት ምስረታውን አከናውኗል።
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ነገ ረቡዕ መስከረም 20 በሚያደርገው መስራች ጉባኤ፤ በተመሳሳይ መልኩ የክልሉን አዲስ መንግስት ይመሰርታል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ምስረታ እና የመክፈቻ ጉባኤ የሚካሄደውም በዚሁ ቀን ነው።
ከነገ በስቲያ ሐሙስ ጉባኤያቸውን የሚያደርጉት የሲዳማ እና የአማራ ክልል ምክር ቤቶች፤ በዚያኑ ዕለት አዲስ መንግስት መስርተው ርዕሰ መስተዳደሮቻቸውን ይመርጣሉ። የሁለቱ ክልሎች ምክር ቤቶች ጉባኤዎች የሚካሄዱት በሀዋሳ እና ባህር ዳር ከተሞች ነው።

በስድስተኛው የምርጫ ዘመን በክልልነት የተመሰረቱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ምክር ቤቶች፤ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መስራች ጉባኤያቸውን የሚያካሄዱት በተመሳሳይ ቀን ነው። በወልቂጤ፣ አርባ ምንጭ እና ታርጫ ከተሞች የሚካሄዱት የምክር ቤቶቹ ጉባኤዎች፤ ከሐሙስ መስከረም 21 እስከ አርብ መስከረም 22 ድረስ ይቆያሉ።
መጪውን አርብ ለጉባኤ ማካሄጂያነት የመረጡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የሀረሪ ክልሎች፤ በዚሁ ቀን አዲሱ መንግስታቸውን በአሶሳ እና በሐረር ከተሞች ይመሰርታሉ። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መስራች ጉባኤ የሚካሄደውም አርብ መስከረም 22 ነው።
በተመሳሳይ ቀን መስራች ጉባኤውን የሚጀምረው የአፋር ክልል ምክር ቤት፤ በሰመራ ከተማ የሚያካሄደው ስብሰባ እስከ ቅዳሜ መስከረም 23 ድረስ እንደሚቆይ አስታውቋል። ምርጫ ባልተደረገበት ትግራይ ክልል፤ የምክር ቤት መስራች ጉባኤ አይካሄድም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




































