በሰሜን ኢትዮጵያ የአውሮፕላን በረራዎች እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች መቋረጥ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን “በብርቱ ሁኔታ መገደቡን” ተመድ አስታወቀ  

ወደ ትግራይ ክልል እና ወደ ተወሰኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎች እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች መቋረጥ፤ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን “በብርቱ ሁኔታ ገድቦታል” ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ። በዋና ዋና መንገዶች ላይ እየተተገበሩ ያሉ ገደቦች፤ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን፣ የእርዳታ አቅርቦቶችን እና የሰዎችን ከቦታ ቦታ መዘዋወር ማቀቡን ድርጅቱ ገልጿል። 

ይህ የተገለጸው፤ የተመድ ዋና ጸሀፊ ቃል አቃባይ ስቴፈን ዱጃሪች ትላንት ሰኞ መስከረም 18፤ 2019 ምሽት በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ከሱዳን እስከ የመን፣ ከዩክሬን እስከ ቬኒዙዌላ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮች በተነሱበት በትላንቱ የግማሽ ሰዓት ገደማ መግለጫ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሌሎች ሀገራት ቅድሚያ ተሰጥቶታል።

የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደተነሳበት እንዳለፈው አርብ ጋዜጣዊ መግለጫ ሁሉ ትላንትም፤ ተመድ በሀገሪቱ “ውጥረቶችን ለማርገብ” እና “ውይይት ለማድረግ” የሚያስችሉ ሁሉንም ጥረቶችን መደገፍን በተመለከተ እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠቅሷል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ከፌደራል እና ከክልል “አገናኞች” ጋር ግንኙነት እያደረጉ ያሉት የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጉዋንግ ኮንግ መሆናቸውን ቃል አቃባዩ በድጋሚ ተናግረዋል።

ልዩ ልዑኩ ለሰሜን ኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ መፍትሔ ለማፈላለግ፤ ከአፍሪካ ህብረት እና ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር “በቅርበት በመተባበር” እየሰሩ መሆኑንም ዱጃሪች በትላንቱ መግለጫቸው ላይ መልሰው አንስተዋል። ቻይናዊው ጉዋንግ ኮንግ የጀመሩት ጥረት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ግን ቃል አቃባዩ በዝርዝር ከማብራራት ተቆጥበዋል።

ዱጃሪች በትላንቱ መግለጫቸው ይበልጡኑ ጊዜ የሰጡት ለሰብአዊ ጉዳዮች ናቸው። በሰሜን ኢትዮጵያ “እየተባባሰ ያለው የጸጥታ ሁኔታ”፤ የሰብአዊ እርዳታ እንቅስቃሴዎችን እያሰናከለ መሆኑን የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትን (OCHA) ዋቢ በማድረግ ቃል አቃባዩ አስታውቀዋል።

የአውሮፕላን በረራዎች እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች መቋረጥም፤ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን “በብርቱ ሁኔታ መገደባቸውን” ዱጃሪች ተናግረዋል። እነዚህ ክስተቶች የተስተዋሉት በትግራይ ክልል እና በተወሰኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች እንደሆነም የተመድ ዋና ጸሀፊ ቃል አቃባይ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች፣ የእርዳታ አቅርቦቶች እና ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወሩ በዋና ዋና መንገዶች ላይ ያሉ የተጣሉ ገደቦች እንቅፋት መሆናቸውንም ዱጃሪች በትላንቱ መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል። መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው አርብ ባወጣው መግለጫ፤ በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በትግራይ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ስፍራዎች የተቀሰቀሱት “የትጥቅ ግጭቶች” በዜጎች “ከቦታ ቦታ የመዘዋወር” መብት እና በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ” መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ግጭቱን ተከትሎ መግለጫ ያወጡ ሀገራት እና ድርጅቶች፤ በግጭቱ እየተሳተፉ ያሉ ወገኖች የሲቪሎች ጥበቃ እና የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ዱጃሪች በትላንቱ መግለጫቸው፤ “የሰብአዊ ቁሳቁሶች እና የእርዳታ ሰራተኞች በሚፈለጉባቸው ቦታዎች ሁሉ፤ ሁሉም ወገኖች ያልተገደበ ተደራሽነትን እና ደህንነታቸውን ማረጋገጣቸው አሁንም ወሳኝ ነው” ሲሉ  አጽንኦት ሰጥተዋል።  

ግጭቶቹ ባለባቸው ቦታዎች “የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቶች” መጨመራቸውን በትላንቱ መግለጫቸው ላይ የጠቀሱት የተመድ ዋና ጸሀፊ ቃል አቃባይ፤ ሆኖም በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የተመድ አጋር ድርጅቶች በገንዘብ ድጋፍ እጥረት ምክንያት ስራዎቻቸውን “እንዲያቀርጡ” አሊያም መጠኑን “እንዲቀንሱ” ተገድደዋል ብለዋል። ይህ ሁኔታም በስፍራዎቹ ላይ የሰብአዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶችን ቁጥር ጥቂት እንዲሆን እንዳደረገውም አመልክተዋል።

“የሰብአዊ ቁሳቁሶች እና የእርዳታ ሰራተኞች በሚፈለጉባቸው ቦታዎች ሁሉ፤ ሁሉም ወገኖች ያልተገደበ ተደራሽነትን እና ደህንነታቸውን ማረጋገጣቸው አሁንም ወሳኝ ነው”

የመንግስታቱ ድርጅት አጋሮች በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች እና የሚያስፈልጋቸው የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቶች በተመለከተ “አፋጣኝ ግምገማዎች” ማድረጋቸው ዱጃሪች ጠቅሰዋል። ድርጅቶቹ በግጭት አካባቢዎች ያሉ ሁኔታዎችን መከታተል እንደሚቀጥሉ የገለጹት ቃል አቃባዩ፤ ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች ቀጣይነት ያለው እርዳታ ለማቅረብ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን እያጠናከሩ መሆኑን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)