በሰሜን ኢትዮጵያ በበርካታ ግንባሮች ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በኩል፤ ከፌደራል እና ከክልል “አገናኞች” ጋር ግንኙነት እየተደረገ መሆኑን የአንቶኒዮ ጉተሬዝ ቃል አቃባይ ገለጹ። ልዩ ልዑኩ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመተባበር እየሰሩ መሆኑንም ቃል አቃባዩ ተናግረዋል።
የዋና ጸሀፊው ቃል አቃባይ ስቴፈን ዱጃሪች ይህን የተናገሩት፤ ትላንት አርብ መስከረም 15፤ 2019 በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ዱጃሪች በመግለጫቸው የጠቀሷቸው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ቻይናዊው ጉዋንግ ኮንግ፤ በመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተሾሙት በሐምሌ 2017 ዓ.ም. ነበር።
በተመድ የተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገሉት ኮንግ፤ አሁን ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተባባሰው የጸጥታ ሁኔታ መፍትሔ የማፈላለግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ እያካሄዷቸው ያሉ ግንኙነቶች፤ “በፕሪቶሪያ ማዕቀፍ ስር የሚደረግ ውይይት እንዲቀጥል” የመደገፍ ሚና ያለው መሆኑን ቃል አቃባይ ዱጃሪች አስረድተዋል።

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በተፈረመው የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት መሰረት፤ ውይይት እንደገና እንዲጀመር ከመንግስታቱ ድርጅት በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎች በርከት ያሉ ሀገራት ግፊት እያሳደሩ ይገኛሉ። የሰሜን ኢትዮጵያውን ጉዳይ በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ ከተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ዱጃሪች በትላንቱ መግለጫቸው ጠቅሰዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም፤ በኢትዮጵያ ያሉ ክስተቶችን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ቃል አቃባያቸው ገልጸዋል። ጉተሬዝ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ውጥረቶችን ለማርገብ እና ውይይት ለማድረግ የሚደረጉ ሁሉንም ጥረቶችን ለመደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ በኒውዮርክ ከሚገኙ መሪዎች ጋር ግንኙነት እያደረጉ መሆኑንም ዱጃሪች አክለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት ወደ በርካታ ግንባሮች መስፋፋቱ “በጥልቅ አሳስቦኛል” ብሏል። በግጭቱ “የድሮን ጥቃቶች ጥቅም ላይ መዋላቸው” እና “በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሳቸውን” የሚጠቁሙ መረጃዎች ድርጅቱን “በተለይ እንደሚያሳስቡት” የጉተሬዝ ቃል አቃባይ በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




































