የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና ምክትላቸው ክልሉን እንዲመሩ በድጋሚ ተመረጡ 

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አቶ ሙስጠፋ ሙሀመድን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በክልሉ ርዕስ መስተዳድርነት እንዲቀጥሉ መረጠ። ምክር ቤቱ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 21፤ 2019 በጅግጅጋ ከተማ ባካሄደው መስራች ጉባኤ፤ ምክትላቸው ኢብራሂም ኡስማንንም በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ስልጣናቸው እንዲቀጥሉ አድርጓል። 

የክልሉ ምክር ቤቱ አቶ ሙስጠፋን እና ምክትላቸውን በስልጣናቸው እንዲቀጥሉ የመረጠው፤ “በሙሉ ድምፅ” እንደሆነ የሶማሌ ክልል የኮምዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። ላለፉት ስምንት ገደማ ዓመታት የሶማሌ ክልልን የመሩት አቶ ሙስጠፋ፤ ለረዥም ዓመታት ስልጣን ላይ ከቆዩ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች አንዱ ናቸው። 

አቶ ሙስጠፋ ክልሉን መምራት የጀመሩት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ በነሐሴ 2010 ዓ.ም. ነበር። የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አደም ፋራህ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ሲሾሙ የተኳቸው አቶ ኢብራሂም ለስድስት ዓመታት በስልጣን ቆይተዋል።

አቶ ኢብራሂም በሰኔ 2012 ዓ.ም የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ከመሾማቸው በፊት፤ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ። አቶ ኢብራሂም በፌደራል የኃላፊነት ቦታ ከመሾማቸው በፊት የድሬዳዋ ከተማን በከንቲባነት መርተዋል።

በዛሬው የሶማሌ ክልል መስራች ጉባኤ አቶ ኢብራሂምን በምክትልነት እንዲቀጥሉ በዕጩነት ያቀረቧቸው፤ ርዕስ መስተዳድሩ አቶ ሙስጠፋ ናቸው። በዚሁ ጉባኤ ርዕስ መስተዳድሩ የካቢኔ አባላቶቻቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበውም ጸድቆላቸዋል።

በምክር ቤቱ የጸደቀው የክልሉ ካቢኔ፤ የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊውን ጨምሮ በአጠቃላይ 27 ተሿሚዎችን ያካተተ ነው። ከ26 የቢሮ ኃላፊዎች መካከል ስድስቱ ሴቶች ናቸው። 

በዛሬው ሹመት በክልሉ ምክር ቤት የክልሉ መንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ መሀመድ ሻሌ፤ በያዙት የኃላፊነት ቦታ እንዲቀጥሉ ሆነዋል።  አቶ መሀመድ የሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊም ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)