ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ መስከረም 12 እስከ አርብ መስከረም 15፤ 2019 ድረስ ባሉት ቀናት፤ የኮረም እና አላማጣ ሆስፒታሎች ከ420 በላይ የጦርነት ቆስለኞችን መቀበላቸውን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (MSF) አስታወቀ። በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ሽረ ከተማ በሚገኘው ስሁል ሆስፒታል፤ ባለፈው አርብ ብቻ ከ300 በላይ በጦርነት የቆሰሉ ግለሰቦች መድረሳቸውንም ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ገልጿል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ዛሬ ሰኞ መስከረም 18፤ 2019 ባወጣው መግለጫ፤ አሁን ባለው “ወቅታዊ ሁኔታ” ምክንያት የአላማጣ ሆስፒታል እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ይፋ አድርጓል። በዚሁ አካባቢ በጸጥታ ምክንያት የማህበረሰብ አገልግሎትም መቋረጡን ድርጅቱ አመልክቷል።
የግብረ ሰናይ ድርጅቱ “በጦርነት የቆሰሉ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ተመልክቼባቸዋለሁ” ባላቸው ሆስፒታሎች፤ ሰራተኞቹን ተጨማሪ ድጋፍ እንዲሰጡ ማሰማራቱን አስገንዝቧል። ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በዛሬው መግለጫው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉት ግጭቶች ምክንያት “ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል” ላላቸው ታካሚዎች የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ እያቀረበ መሆኑንም ጠቁሟል።
በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በትግራይ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ስፍራዎች “የትጥቅ ግጭቶች” የተቀሰቀሱት ካለፈው ማክሰኞ መስከረም 12 ለሊት ጀምሮ እንደነበር መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ማስታወቁ ይታወሳል። የትጥቅ ግጭቶቹ በዜጎች “በህይወት የመኖር” እና “የአካል ደህንነት” መብቶች ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ” እያሳደሩ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በዛሬ መግለጫው፤ በሽረ ከተማ የሚገኘው ስሁል ሆስፒታል ለሚያስተናግደው ከፍተኛ ቁጥር ላለው ህክምና ፈላጊ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጿል። ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በሽረ፣ ሽራሮ እና ኮረም ከተሞች ባሉ ሆስፒታሎች፤ የእናቶች እና ህጻናት ጤናን ጨምሮ ለጤና ክብካቤ እንቅስቃሴዎች የሚያደርገውን ድጋፍ መቀጠሉንም አክሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































